የሀገር ውስጥ ዜና

ሺህ ጠላት ቢሰበሰብ የኢትዮጵያን ጉዞ ለአፍታም አያስቆመውም – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

By Hailemaryam Tegegn

June 09, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሺህ ጠላት ቢሰበሰብ የኢትዮጵያን ጉዞ ለአፍታም አያስቆመውም አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡

በወልድያ ከተማ በአመራሩና በሕዝቡ ትብብር በአንድነት የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተመርቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ የኢትዮጵያ ጉዞ ወደፊት በመሆኑ ጠላት የፈለገውን ያህል ቢያቅድ ከጉዟችን እንደማያስቆመን ወልድያ ምስክር ናት ብለዋል።

ዛሬ በታሪካዊቷና በየጁዎች ሥልጣኔ መገኛ በሆነችው ወልድያ ከተማ በመገኘት አመራርና ሕዝብ በአንድነት ተግቶ ያሳካቸውን የልማት ፕሮጀክቶች መርቀናል ነው ያሉት።

ወልድያ የልማት፣ የፅናትና የድል አምባ ናት ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከተማዋን የማዘመን፣ የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከላትን እውን የማድረግና የኮሪደር ልማትን የማስፋፋት ሥራዎች ወደፊት የመገስገስ ማረጋገጫዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የእኛ መንገድ መደመር፣ ግባችን ደግሞ ብልጽግና ነው ያሉ ሲሆን፥ ትግላችን መንገዳቸውን ክፍፍል እንዲሁም ግባቸውን ድህነት ካደረጉ ቆሞ ቀሮች ጋር በመሆኑ የኢትዮጵያን ልዕልና ሳናረጋግጥ አንቆምም በማለት አጽንኦት ሰጥተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፥ ሺህ ጠላት ቢሰበሰብ የኢትዮጵያን ጉዞ ለአፍታም አያስቆመውም ነው ያሉት፡፡