የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በሚያስችሉ ስራዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው

By Adimasu Aragawu

June 10, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያስችሉ የሪፎርም ስራዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ትምህርት ቢሮ።

በክልሉ “የዘመነ ፈተና አስተዳደር ስርዓት፤ ለላቀ የትምህርት ጥራት” በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀ የ2018 ዓ.ም ሀገራዊና ክልላዊ ፈተና አስተዳደር ምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በዚህ ወቅት÷ ባለፉት ዓመታት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያስችሉ የሪፎርም ስራዎች ላይ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

የትምህርት ስርዓቱን ለማሻሻል በርካታ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ ጥራት ያለው ትምህርት ለማቅረብ ጥራት ያለው የምዘና ስርዓት ውስጥ ማለፍ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ለዚህም የፈተና ምዘና እና የፈተና አስተዳደር ሥርዓት ማዘመን አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።

በዘንድሮው ክልላዊ ፈተና የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል 89 ሺህ 538 ተማሪዎችን ለማስፈተን ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

‎የሀገር አቀፍ እና ክልል አቀፍ ደረጃ የሚሰጡ ፈተናዎችን ከኩረጃ የጸዳ እንዲሆኑ እና ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን መቻሉም ተገልጿል።

በመድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾን (ዶ/ር) ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች መገኘታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል ገልጿል።