የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል በመጪው ክረምት ሊከሰት የሚችልን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል እየተሰራ ነው

By sosina alemayehu

June 10, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በክልሉ በመጪው ክረምት ሊከሰት የሚችልን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው አለ፡፡

የኮሚሽኑ ም/ኮሚሽነር ሰርክአዲስ አታሌ እንዳሉት÷ በቀጣዩ የክረምት ወቅት በጎርፍ መጥለቅለቅ ምክንያት ሊደርስ የሚችልን ጉዳት ለመከላከል 157 ሚሊየን ብር በጀት ተመድቦ እየተሠራ ነው።

በባለፈው ዓመት በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸው÷ ለአብነትም ቁጥራቸው ከ200 ሺህ በላይ የማሕበረሰብ ክፍሎችን ከጎርፍ አደጋ መጠበቅ የሚያስችል ሥራ መከወኑን ጠቅሰዋል።

በተያዘው ዓመት ደግሞ በክልሉ ዘጠኝ ዞኖች እና 16 ወረዳዎች የጎርፍ አደጋ መከላከል ሥራ እንደሚሠራ ነው ያስረዱት፡፡

ምክትል ኮሚሽነሯ በሚሠሩ የጎርፍ አደጋ የመከላከል ሥራዎች ላይ አጋር አካላት እና የማሕበረሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውንም አሚኮ ዘግቧል።