አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ቬትናም ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት በማከናወኗ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፋለች፡፡
የቬትናም ውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ሌ አን ቱዋን ባስተላለፉት መልዕክት ፥ ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አካታች፣ ሰላማዊ፣ ተአማኒ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ አከናውናለች ብለዋል፡፡
ምርጫው በስኬት በመከናወኑም ለኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በምርጫው በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የወደፊት ዕድላቸውን ለመወሰን ያሳዩት ንቁ ተሳትፎ የኢትዮጵያን እያደገ የመጣ ዴሞክራሲ ብስለት በግልጽ እንደሚያሳይ አውስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የእድገትና የመረጋጋት ተምሳሌት እየሆነች ባለችበት በዚህ ወቅት ቬትናም አስተማማኝ አጋር በመሆን አብራ እንደምትቆም አረጋግጠዋል፡፡
አዲስ አባባን እና ሃኖይን በቀጥታ ከሚያገናኘው የአየር በረራ ጀምሮ ትልቅ እመርታ እያሳየ ካለው ንግድ ልውውጥ ድረስ የሀገራቱ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ከምንጊዜውም በላይ እየጠነከረ መምጣቱ ተመላክቷል፡፡
በኢትዮጵያና ቬትናም መካከል ያለው የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ጠንካራ የወዳጅነት ትስስር አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡
የኢትዮጵያ እና ቬትናም የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተመሠረተበት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በሃኖይ ከተማ በደማቅ ሁኔታ መከበሩን በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡