ቴክ

የዲጂታል ፋይናንስና የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀልን ለመከላከል..

By Melaku Gedif

June 10, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዲጂታል ፋይናንስና የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀልን ለመከላከል ከፍትሕና የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው አለ ኢትዮ ቴሌኮም፡፡

“የኢትዮ ቴሌኮም እና የፍትሕ ተቋማት ጥምረት ለዲጂታል ኢትዮጵያ ደህንነት” በሚል መሪ ሃሳብ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡

መድረኩ በዲጂታል ፋይናንስና የቴሌኮም ማጭበርር እንዲሁም መሰረተ ልማት ላይ እየደረሰ ባለው ጉዳትና መፍትሄዎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ሌጋል ኦፊሰር ለማ ተሰማ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በቴሌኮም ዘርፍ የተገኘውን ስኬት ለማስቀጠል ኩባንያው የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ለተግባራዊነቱ እየተጋ ይገኛል ።

ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ የሆኑት የቴሌኮምና የዲጂታል አገልግሎቶች አካታች ሀገራዊ ልማትን በማፋጠን በኩል ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን ጠቅሰው÷ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደመቀጥል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ቀጣይ መዳረሻ እና ዲጂታል መፃዒ ዕድል የተሳካ ለማድረግ የሶስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ በመቅረጽ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

አዲሱ ስትራቴጂ “አድማስ ዲጂታል” ኢትዮ ቴሌኮምን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እና በዲጂታል የጎለበተ ኩባንያ ለማድረግ ያለመ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ሀገራዊ የልማት አጀንዳዎችን በማፋጠን፣ በቀጣናውና በዓለም አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ አዳዲስ ዕድሎችን ለመክፈት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

በኩባንያው ያለፉት ዓመታት ስኬታማ ግስጋሴ ውስጥ የዲጂታል ፋይናንስና የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሎች እንዳጋጠሙ መጥቀሳቸውን የተቋሙ መረጃ አመልክቷል፡፡

በቴሌኮም መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀም ዘረፋና ስርቆት ሌላኛው ችግር ነው ያሉት አቶ ለማ÷ እነዚህን ወንጀሎች ለመከላከል በተለይም ከፍትሕ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡