አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የበጋ መስኖ ልማት በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው አሉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲ ።
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቂምቢቢት ወረዳ በ21 ሺህ 463 ሄክታር መሬት ላይ የለማ የመስኖ ስንዴ ሰብል ስብሰባ ተጀምሯል።
አቶ አወሉ አብዲ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የበጋ መስኖ ሰብል ልማት በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እያገዘ ይገኛል።
በኦሮሚያ ክልል እየተከናወነ የሚገኘው የበጋ መስኖ ልማት ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር እንዲሁም የአርሶ አደሩን ገቢ በዕጥፍ እያሳደገ መሆኑን ተናግረዋል።
የልማት ሥራው ግብርናውን ለማሸጋገር ጭምር እያገዘ መሆኑን ጠቅሰው÷ የግብርና ሜካናይዜሽን ግብዓቶችን በብዛት፣ በጥራት እንዲሁም ፈጠራን መጠቀም እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በኢኒሼቲቭ መልክ እየተካሄደ ሲሆን÷ይህም በክረምት ዝናብ ብቻ ተወስኖ የነበረው የግብርና ባህል መለወጥ እያስቻለ ነው ብለዋል።
በዚህ ወቅት የክልሉ አርሶ አደር በሁሉም የልማት ወቅቶች የግብርና ሥራን እያከናወነ ነው፤ የገጠር ልማትን ከመሠረቱ ለመቀየር የተጀመረው ስራ ይጠናከራል ነው ያሉት።
በዞኑ በትራክተር ማረስና በኮምባይነር ሰብል የመሰብሰብ ባህል እየተለመደ መጥቷል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡