አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን በዳኝነት እንዲመራ ተመርጦ አሜሪካ እንዳይገባ የታገደው ሶማሊያዊ ዳኛ ኦማር አርታን ወደ ሀገሩ ሲመለስ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡
የ2026 ዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን በዳኝነት እንዲመራ የተመረጠው ሶማሊያዊ ዳኛ ኦማር አርታን በመርሐ ግብሩ ለመታደም ወደ አሜሪካ አቅንቶ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በዓለም ዋንጫ የመጀመሪያው ሶማሊያዊ ዳኛ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ኦማር አርታን አሜሪካ ሲደርስ ያልጠበቀው ነገር ተከሰተ፡፡
በፈረንጆቹ 2025 የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ዳኛ የተባለው ኦማር ማያሚ አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሰ በኋላ ወደ አሜሪካ መግባት እንደማይችል ተነግሮታል፡፡
እድል ያልቀናው ኦማር አርታን ወደ እናት ሀገሩ ሶማሊያ ሲመለስም የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ በቤተ መንግሥታቸው ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል፡፡
በተጨማሪም ለዳኛ ኦማር አርታን ሌሎች የሀገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች እና የሞቃዲሾ ከተማ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል በማድረግ አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ ዳኛ ኦማር እስካሁን ላሳየው ስኬት እንዲሁም ለሀገሩ ላበረከተው አስተዋጽኦ አመስግነዋል፡፡
በቀጣይ ለሚያከናውነው ሥራ ከጎኑ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡
ፊፋ የአሜሪካ ባለስልጣናትን በጉዳዩ ላይ ካነጋገረ በኋላ ዳኛው በውድድሩ ላይ በዳኝነት እንደማይሳተፍ ይፋ ማድረጉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡