የሀገር ውስጥ ዜና

1 ሺህ 8 የምርጫ ክልል ውጤቶች ወደ ማረጋገጫ ማዕከል ደርሰዋል – ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

By Yonas Getnet

June 10, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ1 ሺህ 139 የምርጫ ክልል ውጤቶች 1 ሺህ 8 ያህሉ ወደ ማረጋገጫ ማዕከል ደርሰዋል አሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ።

የቦርዱ ሰብሳቢዋ ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ ከ501 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች 446ቱ እና ከ638 የክልል ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች 562ቱ ወደ ቦርዱ ማረጋገጫ ማዕከል መድረሳቸውን አስታውቀዋል።

ቀሪዎቹ 131 የምርጫ ክልል ውጤቶች በርቀትና በመንገድ ሁኔታ ምክንያት በጉዞ ላይ እንደሆኑ እና በፍጥነት ወደ ማዕከል እንዲደርሱ ቦርዱ ክትትል እያደረገ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ካምፖችና በወታደራዊ ካምፖች የተካሄደው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት መጠናቀቁን ጠቁመው÷ ውጤቶቹን ወደ ማዕከል ለማድረስ የማዳመር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በምርጫው ሂደት ላይ የቀረቡ ቅሬታዎችን በተመለከተም በአጠቃላይ 120 የምርጫ ክልሎች ላይ በፓርቲዎችና በግል እጩዎች ቅሬታዎች መቅረባቸውን አስታውቀዋል።

በቦርዱ የተመደቡ የሕግ ባለሙያዎች ቅሬታዎቹን በማጣራት እንዲሁም ሰነዶችንና ምስክሮችን በመመርመር ላይ እንደሚገኙ ገልጸው÷ በቀረቡ ማስረጃዎች መሰረት ውሳኔ እንደሚሰጥ አስረድተዋል።

ቅሬታ የቀረበባቸው 120 የምርጫ ክልሎች ጉዳይ ከተጣራ በኋላ የምርጫውን አጠቃላይ ውጤት በይፋ ማረጋገጥ እንደሚቻል የቦርዱ ሰብሳቢዋ አመልክተዋል።

በዮናስ ጌትነት