ስፓርት

በድጋሚ በዓለም ዋንጫ መክፈቻ የሚገናኙት ብሔራዊ ቡድኖች – ሜክሲኮ ከደቡብ አፍሪካ

By Melaku Gedif

June 11, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋራ ያዘጋጁት የ2026 የዓለም ዋንጫ ውድድር ዛሬ ምሽት በይፋ መካሄድ ይጀምራል፡፡

በጉጉት የሚጠበቀው የዘንድሮ የዓለም ዋንጫ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስት ሀገራት የሚያዘጋጁት ውድድር ነው፡፡

በ2026ቱ ዓለም ዋንጫ መርሐ ግብር 48 ሀገራት የሚሳተፉ ሲሆን ÷ በዚህም 104 ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡

በዘንድሮ የዓለም ዋንጫ በአጠቃላይ 1 ሺህ 248 ተጫዋቾች በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ይሆናል፡፡

በመድረኩ በርካታ ከዋክብት የመጨረሻቸው የዓለም ዋንጫ ውድድር ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

እስካሁን ድረስ 8 ሀገራት ብቻ የዓለም ዋንጫያሸነፉ ሲሆን ÷ ብራዚል፣ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ አርጀንቲና፣ ፈረንሳይ፣ ኡራጓይ፣ እንግሊዝ እና ስፔን በመድረኩ ሻምፒዮን መሆን የቻሉ ሀገራት ናቸው፡፡

የ2026 ዓለም ዋንጫ ውድድር ዛሬ በይፋ ሲጀምር ከአዘጋጆቹ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነቸው ሜክሲኮ ምሽት 4 ሰዓት ከደቡብ አፍሪካ ትገናኛለች፡፡

ሜክሲኮ ለ18ኛ ጊዜ ተጋጣሚዋ ደቡብ አፍሪካ ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ በመድረኩ የሚሳተፉ ይሆናል፡፡

ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በፈረንጆቹ 2010 ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ውድድር የመክፈቻ ጨዋታ ላይ መገናኘታቸው ይታወሳል፡፡

በወቅቱ ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ያደረጉት የመክፈቻ ጨዋታ አንድ አቻ የተጠናቀቀ ሲሆን÷ ሸበላላ ለደቡብ አፍሪካ ያስቆጠራት ግብ አስደናቂ እንደነበረች አይዘነጋም፡፡

የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ሜክሲኮ ከደቡብ አፍሪካ ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሚያደርጉት ጨዋታ ጅማሮውን ያደርጋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ