አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገዳ ሥርዓት የሕዝብን የስልጣን ባለቤትነት መብት ያረጋገጠ ነው አሉ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረህማን።
71ኛው የቱለማ ገዳ ሥርዓት የአለንጌ (ስልጣን) ርክክብን አስመልክቶ በዓድዋ ድል መታሰቢያ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
ወ/ሮ ሰዓዳ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የገዳ ሥርዓት የሕዝብን በራስ የማስተዳደር መብት በማረጋገጥና የፖለቲካ ስልጣንን በመምራት ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል፡፡
ገዳ የኦሮሞ ሕዝብ ለሀገርና ለዓለም ያበረከተው ሥርዓት መሆኑን አውስተው÷ ያለምንም ራስ ወዳድነትና ግጭት ስልጣን በሰላማዊ መንገድ የሚሸጋገርበት ሥርዓት መሆኑን አስረድተዋል።
አላንጌውን ለማስረከብ ዋዜማ ላይ የሚገኘው የቱለማ ገዳ እያደገና እየበለጸገ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
አባቶች ተንከባክበውና ጠብቀው እዚህ ያደረሱትን የገዳ ሥርዓት አዲሱ ትውልድ እሴት በመጨመር ለታሪክ ማስቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ከሰኔ 4 እስከ 7 ቀን 2018 ዓ.ም በተለያዩ ሁነቶች የሚካሄደው የቱላማ ገዳ ስልጣን ሽግግር ሥነ ሥርዓት የገዳ ስልጣን ከገዳ ሜልባ ወደ ገዳ ሙደና የሚሸጋገርበት ነው፡፡
በፀሐይ ጉሉማ