አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ ለጫናዎች ሳይበገር በድምጹ ዴሞክራሲን ለማጽናት ያለውን ፍላጎት አሳይቷል አሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፡፡
በክልሉ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አፈጻጸም እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የግምገማ መድረክ ተካሂዷል።
አቶ ጥላሁን በዚህ ወቅት እንዳሉት÷7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ አካታችና ነጻ በሆነ መልኩ ተካሂዷል፡፡
ለዚህም በቅድመ ምርጫ የተከናወኑ የቅንጅት ሥራዎችና ብቃት ያለው የአመራር ሥርዓት መዘርጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበረከቱን ተናግረዋል፡፡
ሕብረተሰቡ ጸሐይ፣ ብርድ እና ረጃጅም ሰልፎች ሳይበግሩት በድምጹ ዴሞክራሲን ለማጽናት ላሳየው ተጋድሎ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በክልሉ ምርጫው በሰላም ለመጠናቀቁ የአመራሩ፣ የአባላትና የደጋፊዎች ቅንጅት ውጤት ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው አመልክተዋል፡፡
በቅድመ ምርጫ የታየውን ጽናትና ርብርብ በድህረ ምርጫ ተግባራት ላይ መድገም እንደሚገባ አጽንኦት መስጠታቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡