አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምርጫውን በማሸነፍ መንግሥት የሚመሰርተው የፖለቲካ ፓርቲ የመራጩን ሕዝብ ፍላጎት ለመመለስ መስራት አለበት አሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች።
ነዋሪዎቹ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት÷ አሸናፊው ፓርቲ የተጀመሩ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን በማስቀጠል፣ ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር እና አስተማማኝ ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
የከተማዋ ነዋሪ ሂሩት ጎሽሜ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በምርጫ ማግስት ላይ መገኘቷን አስታውሰው÷ ወደፊት ስልጣን የሚረከበው አካል ሙሉ ትኩረቱን ለሀገርና ለዜጎች በሚጠቅሙ ስራዎች ላይ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።
የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፣ ወጣቶች በስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ረገድ ትልቅ ኃላፊነት አለበት ብለዋል።
ዜጎች ከተራ ማማረር ወጥተው የሰላም አምባሳደር መሆን እንዳለባቸውና ሁሉንም ነገር ከመንግሥት ብቻ የመጠበቅ ልማድ ሊቀየር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ጸሐይነሽ ማሞ በበኩላቸው÷ አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ሀገርን በሰላም፣ በፍቅር እና በሕብረት ወደፊት ሊመራ ይገባል ብለዋል።
በተለይም የሴቶችና ህጻናት መብት እንዲሁም እኩልነት እንዲጠበቅ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድል ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ ጠቁመው÷ ይህንንም ለማሳካት ሕዝብና መንግሥት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
አቶ ብርሃኑ ከማል የትኛውም ፓርቲ ለስልጣን ቢበቃ ከዜጎች ጋር በቅርበት በመተባበር ሀገርን በታማኝነት ማገልገል እንዳለበት ገልጸዋል።
አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ጠንካራ የልማት እና የሰላም ስራዎች ላይ በማተኮር ኢትዮጵያን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እንዲሰራም ጠይቀዋል።
በዮናስ ጌትነት