አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን ከ989 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ ተችሏል አለ፡፡
ከዚህም ውስጥ 969 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የሚገመቱ የገቢ እንዲሁም 20 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች መሆናቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
የኮንትሮባንድ እቃዎቹ የተያዙት ኮሚሽኑ ከፌደራልና ከክልል የፖሊስ ተቋማት እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ባደረገው ክትትል መሆኑን ገልጿል፡፡
ከኮንትሮባንድ ቁሳቁሶች በተጨማሪ የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 16 ተጠርጣሪዎችና 21 ተሽከርካሪዎች መያዛቸው ነው የተገለጸው፡፡
በዚህም አዳዲስና ልባሽ ጨርቆች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የግንባታ እቃዎች፣ ቡና፣ ጥራጥሬ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ መድኃኒት፣ ማዕድናት፣ የቁም እንስሳትና የውጭ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡
ኮንትሮባንድ በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመከላከል ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ኮሚሽኑ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡