አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ እና ኢራን የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረባቸው በሚነገርበት በዚህ ወቅት በሆርሙዝ ወሽመጥ አቅራቢያ ወታደራዊ ጥቃት መፈጸሙ ተመላክቷል፡፡
በዚህም የአሜሪካ ጦር ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ በማምራት ላይ የነበሩ በርካታ የኢራን አጥፎቶ ጠፊ ድሮኖችን መትቶ መጣሉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
አሜሪካ በኢራን ድሮኖች ላይ ርምጃ መውሰዷን ያረጋገጠች ሲሆን ÷ ጥቃቱ የተፈጸመውም ድሮኖቹ በንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ ላይ ስጋት በመደቀናቸው ነው፡፡
በሌላ በኩል በወቅቱ ከኢራን ጦር ፈቃድ ውጭ በወሽመጡ ለመሻገር ለሞከሩ መርከቦች የማስጠንቀቂያ ተኩስ ተሰጥቶ እንደነበር የኢራን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
በመካከላቸው የነበረውን ጦርነት ለማቆም የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረባቸውን ያሳወቁት አሜሪካ እና ኢራን በመጪዎቹ ቀናት ውስጥ የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት እንደሚፈርሙ ይጠበቃል።
ስምምነቱ የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት የሚያስችል ሲሆን ÷ አሜሪካ የታገዱ የኢራን ሃብቶችን እንደምትለቅ እና በነዳጅ ኤክስፖርት ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችም እንደሚነሱ ተጠቁሟል።
የኢራን የኒውክሌር መርሐ ግብርን በተመለከተ በሚቀጥሉት 60 ቀናት ውይይት እንደሚደረግ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ምንጮች ዋቢ አድርጎ ሬውተርስ አስነብቧል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል የድርድሩ አካል እንዳልነበረች እና ለደህንነቷ ስትል ወታደራዊ ርምጃዎቿን የመቀጠል ነጻነት እንዳላት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንሁ አስታውቀዋል፡፡
በዮናስ ጌትነት