አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከአምስቱ የኦሮሞ ገዳዎች አንዱ የሆነው የቱለማ ገዳ የ71ኛው ዙር የስልጣን ርክክብ ማጠቃለያ በነገው ዕለት በዳካ ኮራ አርዳ ጂላ ይካሄዳል።
የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት ለብዙ ዘመናት የዘለቀና ዓለም ያደነቀው የማይዳሰስ ቅርስ ሲሆን፥ የማኅበረሰቡን ባህል፣ እሴትና ሥነ ምግባር ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ በማሻገር ረገድ ትልቅ ሚና እየተወጣ ነው።
የገዳ ሥርዓት ሰላምና እርቅን የሚያሰፍን፣ የማኅበረሰቡን ተሳትፎ የሚያጠናክር፣ ማንነት እና ባህልን የሚጠብቅ፣ እኩልነትን የሚያረጋግጥ እንዲሁም ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን ለትውልድ የሚያስተምር መሆኑን የተለያዩ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
በአሁኑ ወቅትም የቱለማ ገዳ ሥርዓት የ71ኛውን ዙር የሥልጣን ሽግግር እያካሄደ ሲሆን፥ የስልጣን ወይም የአለንጋ ሽግግር የማጠቃለያ መርሐ ግብር በነገው ዕለት ባሕላዊ ስርዓቱን በተከተለ መንገድ ይካሄዳል።
በዚህ የሥልጣን ሽግግር የቱለማ ኦሮሞ ገዳ ከ’ገዳ ሜልባ’ ወደ ‘ገዳ ሙደና’ ለማስተላለፍ በ’ዳካ ኮራ’ የባህል ስፍራ የተለያዩ ባህላዊ ሥነ ሥርዓቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በዚህ ሥርዓት ላይ ሥልጣን ለሚረከቡት አካላት ቦኩ ወይም የሥልጣን ማሳያ የሆነውን በትር እና አለንጋ ይረከባሉ።
ባህላዊ ግብዣዎች፣ ምርቃት፣ የሕዝባዊ ባህል ዜማዎችና ውዝዋዜዎች በሚቀርቡበት የስልጣን ሽግግር መርሐ ግብር ላይ የኦሮሞ ሕዝብ አዲሱን አባ ገዳ በደስታ ይቀበላል፡፡