አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ የበርካታ ከያኒያን መፍለቂያ ከተማ ብትሆንም ሙያተኞችን እና ታዳሚውን የሚመጥን የጥበብ መመልከቻና መታደሚያ ስፍራ እምብዛም አልነበራትም።
ከለውጡ በፊት የነበሩ ቴአትር እና ሲኒማ ቤቶች እርጅና የተጫናቸው ከመሆናቸው በተጨማሪ የጥበብ ቤተሰቦችን የማይመጥኑ ነበሩ። ከለውጡ በኋላ በተከናወነው ዘርፈ ብዙ የልማት ስራ በተለይም በከተማዋ በሚከናወኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት በርካታ አምፊ ቴአትር ቤቶችና ሲኒማ ቤቶች መገንባት ተችሏል።
ለአብነትም በቅርቡ ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለሕዝብ ክፍት የተደረጉ የህፃናት እና ወጣቶች ቴአትር ቤት እንዲሁም የአዲስ ሲኒማ ኮንፕሌክስ እና በዓድዋ ሙዚየም ውስጥ የሚገኘው ስማርት ሲኒማ ቤትን ጨምሮ በተለያዩ የከተማ አካባቢዎች የተገነቡ ታላላቅ ሁነቶቸን ማስተናገድ የሚችሉ ግዙፍ ስፍራዎች ለዚህ አይነተኛ ማሳያ ናቸው፡፡
የእነዚህ አንፊ ቴአትር እና ሲኒማ ቤቶች ግንባታ ለጥበበኞች የፈጠራ መፍለቂያ ከመሆን ባለፈ በኢትዮጵያ የኪነጥበብ ኢንዱስትሪ አዲስ ታሪክ መፃፍ የቻሉ እንዲሁም ከያኒያን ስራዎቻቸውን በዓለም አቀፍ ጥራት ለተመልካች ማቅረብ እንዲችሉ ዕድል የከፈቱ ናቸው፡፡
በተጨማሪም ለከተማዋ ነዋሪዎችና ጎብኚዎች ጥበብን በከፍተኛ ጥራትና በምቾት የሚታደሙበት ልዩ መዳረሻ መሆን ችለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልማት ሁለንተናዊ መሆኑን በመገንዘብ አሁንም በሚሰራቸው የልማት ስራዎች ሁሉን አካታችነት ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ በትኩረት መስራቱን እንደሚቀጥል የከተማዋ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል።