የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሉ በአረንጓዴ ዐሻራ ከ300 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው

By Hailemaryam Tegegn

June 15, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዘንድሮው ክረምት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ300 ሚሊየን በላይ ችግኞችን መትከል የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት እንዳስታወቀው ÷ አረንጓዴ ዐሻራ በሁሉም መስክ ምርታማነትን በማሳደግ የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትንና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚያስችል መሠረት እየጣለ ነው፡፡

በክልሉ መርሐ ግብሩ የተፈጥሮ ሚዛኑን የጠበቀ አረንጓዴ ከባቢን ዕውን የማድረግ አስደናቂ ስኬት በማስመዝገብ ላይ መሆኑን አመልክቷል፡፡

ሕብረተሰቡን በንቃት በማሳተፍ የተራቆተ ሥነ ምሕዳር እንዲያገግም የማድረግ እና ምርታማነትን የማሳደግ ውጤታማ ተግባር በመከናወን ላይ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡

ዘንድሮ ለመርሐ ግብሩ ግብ ስኬት በተሰጠው ልዩ ትኩረት በበልግ ከተከናወነው ተከላ በተጨማሪ በክረምት የአረንጓዴ አሻራ ከ300 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል የሚያስችል በቂ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡

ከዚህ ውስጥም 67 ሚሊየን ችግኞች በአንድ ጀንበር የተከላ መርሐ ግብር እንደሚተከሉ ነው የተገለጸው፡፡

በቅድመ ዝግጅቱ በ1 ሺህ 201 ችግኝ ጣቢያዎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ፣ የጥምር ደንና ሌሎች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ችግኞች ዝግጅት በመጠናቅ ላይ መሆኑ ተመላክቷል፡፡