የሀገር ውስጥ ዜና

የዓለም ስጋት የሆነው የፀረ-ተህዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መለመድ

By sosina alemayehu

June 15, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፀረ-ተህዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መለመድ የዓለም ትልቁ ስጋት ሆኗል አለ የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን።

የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የፀረ-ተህዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መለመድ ችግር በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ለ750ሺህ ሰዎች ሞት ምክንያት ይሆናል።

ችግሩ በአዳጊ ሀገራት ከፍ እንደሚል አንስተው÷ ወደ 5 በመቶ የኢኮኖሚ ኪሳራ እንደሚያደርስ ጥናቶች ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል።

አግባብ ያልሆነ የፀረ-ተዋህሲያን መድሃኒቶችን መጠቀም፣ ከትዕዛዝ ውጪ መድሃኒቶችን ጨምሮና ቀንሶ መውሰድ፣ የግልና የአከባቢ ንፅህናን አለመጠበቅ እና መሰል ጥንቃቄ የጎደላቸው ተግባራት ችግሩን ከሚያስከትሉ መንስኤዎች መካከል ናቸው ብለዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሀገር አቀፍ የማህበረሰብ ፋርማሲዎች እንዲቋቋሙ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ ከጤና ሚኒስቴር እና ከሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ የግንዛቤ ማስፋት ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በታምራት ደለሊ