አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አፍሪካም ማሰብ፣ ማቀድና መስራት እንደምትችል ለዓለም የምናሳይበት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ግንባታ ሒደት ያለበትን ሁኔታ ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቁና በሚወጣለት ሀብት እንዲሁም በሚያንቀሳቅሰው ማሽነሪ በአፍሪካ ደረጃም ቢሆን ቀዳሚው ነው ።
በብዙ ሀገራት ብሎም በኢትዮጵያ የሥራ ሐሳብና ሀብት ቢኖርም፥ የፕሮጀክት አመራር ችግር ስላለ ፕሮጀክቶች መቼ ተጀምረው መቼ እንደሚጠናቀቁና እንዴት ቁጥጥር እንደሚደረግባቸው በቂ ግንዛቤ አለመኖሩን አንስተዋል፡፡
አሁን ላይም ይህንን የቆየ ልማዳዊ አሰራር በቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት መቀየር ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በአሁኑ ወቅት በፕሮጀክቱ ከ8 ሺህ በላይ ሠራተኞች እንደሚገኙና እስከ 4 ሺህ የሚጠጉ ማሽነሪዎችና መኪናዎች በ30 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ሌሊትና ቀን እንደሚንቀሳቀሱ አብራርተዋል፡፡
የፕሮጀክቱ እንቅስቃሴ እንደ አንድ ትንሽ ከተማ ማለት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ለማሽኖቹ በቀን ከ650 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ፤ በ10 ቀን ውስጥ ደግሞ ከ6 ነጥብ 5 እስከ 7 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ ጥቅም ላይ እንደሚውል አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን ይህንን ግዙፍ ፕሮጀክት በስኬት ለመምራት የነዳጅ፣ ማሽነሪና ተሽከርካሪ በብቃት ለማስተናገድ ዘመናዊ ሥርዓት መዘርጋቱን አብራርተዋል።
አውሮፕላን ማረፊያውን መገንባት ብቻ ሳይሆን የ4 ሺህ መኪናዎችን ዕለታዊ እንቅስቃሴ በቁጥጥር ማዕከል፣ በዳሽ ቦርድና በድሮን ቴክኖሎጂ የታገዘ ኦፕሬቲንግ ሲስተም በመጠቀም በብቃት ማስተናገድና መረዳት ለአመራሩ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በፕሮጀክቱ ጅማሮ ላይ ብዙዎች አትችሉም፣ ገንዘቡም አይገኝም፣ ስራውን መምራት አይሆንላችሁም፣ ለምን ታስባላችሁ የሚል የተስፋ መቁረጥ ምልከታ እንደነበራቸው አስታውሰው÷ እኛ ደግሞ እንችላለን፤ ይገባናል እያልን ነው፤ ማን እንደሚያሸንፍ ጊዜ ሲደርስ እናያለን ሲሉም አክለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ይህ ኤርፖርት ከዚህ ቀደም እንደነበሩት ፕሮጀክቶች ሳይሆን በከፍተኛ ክትትል የሚመራ በመሆኑ ባልነው ጊዜ እንጨርሰዋለን ሲሉም አረጋግጠዋል።
በሶስና አለማየሁ