የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገር ሉዓላዊነትን የማያስደፍር የሰማይ ላይ ጋሻ ነው – ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

By Adimasu Aragawu

June 16, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገር ሉዓላዊነትን የማያስደፍር የሰማይ ላይ ጋሻ ነው አሉ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ።

ሀገርን ከባዕድ ወረራና ከባንዳዎች ሴራ የሚከላከል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀና የማይበገር አየር ኃይል መገንባቱን የገለጹት ዋና አዛዡ÷ የሀገር ሉዓላዊነትን የማያስደፍር የሰማይ ላይ ጋሻ ሆኗልም ነው ያሉት።

በቴክኖሎጂ የላቀ፣ በሥነ-ልቦና የጠነከረ፣ ለሀገር ክብር መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ የሆነ እና ጠላትን አምርሮ የሚጠላ ጀግና ሠራዊት መገንባቱንም ተናግረዋል።

የአየር ኃይሉ የውጊያ ዝግጁነት ቀዳሚ ዓላማ ውጊያን ከሩቅ ማስቀረት ነው፤ ሆኖም ጠላት የሰላም አማራጭን ችላ ብሎ ወደ ውጊያ ከገባ፣ አየር ኃይላችን የጠላትን ህልውና እስከወዲያኛው የሚያከስም አስተማማኝ መቺ ኃይል መሆኑን በተግባር ያረጋግጣል ብለዋል።

የጦር መሪ ቀዳሚ ኃላፊነት በሰላም ጊዜ ሠራዊቱን ለውጊያ ዝግጁ ማድረግ፣ ጦርነት ካጋጠመም ድል መቀዳጀት እንደሆነ አንስተው÷ ሀገር የምትፀናው በዘመናዊነት በተደራጀ፣ በሰለጠነ፣ በታጠቀና ብቁ በሆነ ጀግና ሠራዊት እንደሆነ አስረድተዋል።

የአየር ኃይሉ ዘላቂ የተቋም ግንባታ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በዲጂታል የሥልጠና አሠራሮች እንዲሁም በዘመናዊ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂዎችና የጦር ትጥቆች የታጀበ መሆኑ ተቋሙን በቀጣናው የማይበገርና አስተማማኝ ኃይል እንዳደረገውም ገልጸዋል።

ጀግኖች አብራሪዎቻችን እና ቴክኒሺያኖቻችን የኢትዮጵያን ሰማይ በንቃት በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ ያሉት ሌተናል ጄኔራል ይልማ÷ ተቋሙ አሁን ላይ በዘመናዊ አውሮፕላኖችና ሄሊኮፕተሮች የታገዘ ፈጣን የኃይል ስምሪት እና የላቀ ሎጂስቲክስ አቅም መገንባቱን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያልሙ ኃይሎች ሰማያችንን ሌት ተቀን በንስር ዓይን የሚጠብቀውና በፅኑ ክንድ የሚቆጣጠረው ጀግናው አየር ኃይል የታሪካዊ ውድቀታቸው ምክንያት እንደሚሆን ሊያውቁት ይገባል ማለታቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።