ፋና ስብስብ

አዲስና ወጥ የተሸከርካሪ ሰሌዳ ለምን …..

By Adimasu Aragawu

June 16, 2026

ኢትዮጵያ የቀድሞውን የተሽከርካሪ ሰሌዳ በማስቀረት፣ ወጥ ሀገራዊ የሰሌዳ ሥርዓትን እየዘረጋች ነው፡፡

የዚህ አሰራር ፋይዳው ብዙ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ጥቅሞቹም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የደኅንነት ናቸው።

ይህም የተሽከርካሪዎችን ማንነት አንድና ወጥ በማድረግ የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ፣ ኢኮኖሚያዊ ቅልጥፍናን መጨመር እና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ቁጥጥርን መዘርጋት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን ሥርዓት በዚህ ዓመት ወደ ሥራ እያስገባች ያለ ሲሆን፣ አሰራሩ የክልል መለያዎችን በማስቀረት በቪየና ኮንቬንሽን መሠረት ለሀገራችን የተሰጠውን ዓለም አቀፍ የ”ETH” / “ኢት” ኮድ እና ኪውአርኮድ መለያዎችን ይዟል፡፡

አዲሱ ሰሌዳ ጠንካራና የረዥም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡ በህትመቱም ከፍተኛ የደህንነት ጥንቃቄ የተደረገበት በመሆኑ ማጭበርበርን ይከላከላል። ሰሌዳው ዘመናዊ ቺፕና የፊት መስታወት ላይ የሚለጠፍ የRFID መለያም አለው፡፡ ይህም የተሽከርካሪውን አሁናዊ መረጃ (Real-time data) በሰከንዶች ውስጥ ለማወቅ ያስችላል። አሰራሩ ተሽከርካሪው የአገልግሎት ለውጥ በሚያደርግበት ጊዜ የማይቀየርና ተጨማሪ ወጪን ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር ነው።

በርካታ የዓለም ሀገራትም ከፌደራሊዝም እና ከፖለቲካዊ አወቃቀራቸው ጋር በማጣጣም ተመሳሳይ ወጥ ሥርዓቶችን ይጠቀማሉ፡፡

እንደ ምሳሌ የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራትን እና ከአህጉራችን የናይጄሪያን እንመልከት፡፡

የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት ጉዳዩን የአንድነትና የኢኮኖሚ ውህደት ምሰሶ አድርገው ይወስዱታል፡፡ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ጣሊያን እጅግ የተማከለ እና ወጥ የሆነ ሰሌዳ ይጠቀማሉ። የተሽከርካሪው ሰሌዳ በግራ በኩል የአውሮፓ ሕብረትን ሰማያዊ ዓርማ እና የሀገሪቱን መለያ ይይዛል፡፡ ይህ አሠራር ተሸከርካሪዎች ያለ ምንም አስተዳደራዊ ወይም ስነ-ልቦናዊ ገደብ ድንበር ተሻግረው በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ እና የንግድ ፍሰቱ እንዲፋጠን አድርጓል። ሁሉም ታርጋዎች በማዕከላዊ የዲጂታል መረጃ ቋት የተገናኙ በመሆናቸው ወንጀልን ለመከላከልና የትራፊክ ሕግ ለማስከበር ምቹ ሆነዋል። የታርጋው መረጃ በቀላሉ በካሜራ የሚነበብ በመሆኑ የሕግ ማስከበሩን ቀላል አድርገውታል፡፡

ናይጄሪያ እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ብሔሮችና የፌደራል ክልሎች ያላት ሀገር ስትሆን፣ ቀደም ሲል የነበሩትን የየግዛቱን የተሽከርካሪ የሰሌዳ ልዩነቶች ለማስቀረት ወጥ የሆነ ሀገራዊ የሰሌዳ ሥርዓት ዘርግታለች።

ይህ የሆነው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ለሀገራችን ለኢትዮጵያም ቢሆን የተሽከርካሪ ሰሌዳ ወጥነት ፋዳው ብዙ ነው፡፡

የመጀመሪያው ሀገራዊ አንድነትን እና ነፃ እንቅስቃሴን ማጠናከር ነው፡፡ ይህም ዜጎችን ከአድልዎ በመጠበቅ፣ የመዘዋወር ነጻነትን በማበረታታት፣ ሀገራዊ የስነልቦና አንድነትን መፍጠር ነው፡፡ በዚሁ መሠረት አሽከርካሪዎች ከተመዘገቡበት ክልል ውጭ ሲጓዙ ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ማንነትን መሠረት ያደረገ ትንኮሳ፣ ጥቃት ወይም አድልዎ ያስቀራል። ዜጎች በማንኛውም የሀገሪቱ ክፍል ያለምንም ሥጋትና መገለል በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ እና እንዲሠሩ ያግዛል። ልዩነትን ከሰሌዳ ላይ ማንሳት በሕዝቦች መካከል የ”እኛ” እና “የእነሱ” ስሜትን በመቀነስ፣ የሀገራዊ አንድነት ስሜትን ያሳድጋል።

ሁለተኛው ጠቀሜታ የሕግ ማስከበር እና የደኅንነት ሥርዓትን ማዘመን ነው፡፡ ሥርዓቱ ወጥ የቁጥጥር አሰራርን ይዘረጋል፤ ወንጀልን ለመከላከል እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ቀላል ለማድረግም ያግዛል፡፡ ይህም ሲባል የጸጥታ አካላት በመላው ሀገሪቱ ያሉ ተሽከርካሪዎችን በቀላሉ በአንድ ዓይነት የዲጂታል የመረጃ ቋት በመጠቀም እንዲቆጣጠሩ ያስችላል። የፍጥነት መቆጣጠሪያ ካሜራዎች እና የትራፊክ መቆጣጠሪያ ሥርዓቶች ሰሌዳዎችን ያለ ምንም ውስብስብ የክልል ኮድ ልዩነት በቀላሉ እንዲያነቡ ያደርጋል። ወንጀለኞች የታርጋ መለያዎችን በመለዋወጥ ወይም ክልላዊ ስሜትን ተጠቅመው ከሕግ ለማምለጥ የሚያደርጉትን ጥረትም ያስቀራል።

ሦስተኛው ኢኮኖሚያዊ እና አስተዳደራዊ ጠቀሜታ ነው፡፡ አሰራሩ የንግድ እና የንብረት ሽያጭ ሂደትን ቀላል ያደርገዋል፡፡ የሰሌዳ ምርት ወጪን በመቀነስ አስተዳደራዊ ቅልጥፍናን መጨመርም ያስችላል፡፡ አንድ ተሸከርካሪ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ሲሸጥ የሚጠይቀውን የታርጋ ቅያሬ፣ ቢሮክራሲ እና አላስፈላጊ ወጪ ያስቀራል እንደማለት ነው። ለመላው ሀገሪቱ አንድ ዓይነት ቅርጽ፣ ቀለም እና ይዘት ያለው ታርጋ ማምረት የዕቃ አቅርቦት እና የህትመት ወጪን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል። የትራንስፖርት መተግበሪያዎች እና መዝገቦች በአንድ ማዕከላዊ የፌደራል ሥርዓት ስለሚመሩ የመረጃ መደራረብን እና የአሠራር መዘግየትንም ያስቀራል።

#Fana_Digital #ፋና_ዲጂታል