የሀገር ውስጥ ዜና

አረንጓዴ ዐሻራ አረንጓዴ ወርቅ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Hailemaryam Tegegn

June 16, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ውጤት አረንጓዴ ወርቅ ነው አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር “ተስፋን መትከል” በሚል መሪ ሀሳብ በትናንትናው ዕለት በቢሾፍቱ ከተማ በይፋ አስጀምረዋል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት፥ የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ አፈርን ከመሸርሸር የመጠበቅ ሥራ ብቻ ሳይሆን የተረበሸን ማንነት የማከምና ሀገራዊ ስነልቦናን የመገንባት እንዲሁም ለትውልድ የሚተላለፍ ታላቅ ተስፋ ነው።

“ተስፋን መትከል” የሚለው የዘንድሮው መርሐ ግብር መሪ ሀሳብ ከሰው ልጅ መንፈሳዊ ዕድገት ጋር የሚያያዝ ሲሆን፥ አረንጓዴ ጸዳል ውስጣዊ ሰላምን የመስጠትና የተረበሸን ማንነት የማከም የተፈጥሮ ጉልበት እንዳለው አብራርተዋል።

መርሐ ግብሩ የገረጣውን ምድር በአረንጓዴ ልብስ ከማልበስ ባለፈ ህዝቡ በአንድ ልቦና ተደምሮ እንዲሰራ በማድረግ የመደመርን ኃይል በተግባር የሚያሳይ የስነልቦና ለውጥ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ውጤት አረንጓዴ ወርቅ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ቢዋቡበት ጌጥ ቢነግዱበት ደግሞ ታላቅ ሀብት መሆኑንም ተናግረዋል።

ለዚህም ከቡና ምርት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ዕድገት ማስመዝገቡንና አዳዲስ የፍራፍሬ ዝርያዎችን በማስተዋወቅ የተገኘውን የምግብ ዋስትና ስኬት በምሳሌነት አንስተዋል።

ይህ አረንጓዴ ውርስ ትውልድ በድህነትና እርዳታ የሚታወቅበትን ታሪክ ቀይሮ በልቶ ጠግቦ ሌላውን ማገዝ የሚችልበትን ብሩህ ነገ ዛሬ የሚስልበት ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በአረንጓዴ አሻራ “አይችሉም” የሚሉ የጥርጣሬ ድምጾችን በተግባር መስበር እንደተቻለና በዚህም ዓለም መደመሙን አንስተዋል፡፡

ይህ “የእንችላለን” ስነልቦና ለቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግዙፍ ግንባታም ትልቅ አርማና አንቀሳቃሽ ኃይል እንደሚሆን አመልክተዋል።

በሶስና አለማየሁ