አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የቀጣይ 90 ቀናት ዕቅዳችንን በልዩ ትኩረት እንፈጽማለን አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ በከተማ አስተዳደሩ የ90 ቀናት የመንግሥትና የፓርቲ ስራዎች ዕቅድ ላይ ተወያይተን ወደ ተግባር አስገብተናል ብለዋል።
በድህረ ምርጫ ሕብረተሰባችን ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል እቅድ ይዘን በልዩ ትኩረት እንፈጽማለን ነው ያሉት።
የተለዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት፣ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋትና የመሶብ አንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎትን ማስፋት ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጳጉሜን 5 በሚቆየው 90 ቀናት ውስጥ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም የስራ እድል ፈጠራ፣ የሴቶችና ወጣቶች ተጠቃሚነት፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት፣ የከተማ ግብርናና የሌማት ትሩፋት፣ የሰላም ግንባታና የገቢ አሰባሰብን ማጠናከር እንዲሁም የንግድ ስርዓቱን መግራት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡
ተረጂነትን መቀነስ፣ የበጎ ፍቃድ መርሐ ግብር ተሳትፎን ማሳደግ፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በአዲስ ቅኝት መምራት ከከተማ አስተዳደሩ የቀጣይ 90 ቀናት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡
የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎችን ጨምሮ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜና በጀት በጥራት ለማጠናቀቅ ተዘጋጅተናል ነው ያሉት።
አዲሱ በጀት ዓመት ህዝባችንን ይበልጥ የምናገለግልበትና አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ጉዟችንን የምናረጋግጥበት እንዲሆን ከእቅድ ዝግጅት እስከ ተግባር አፈፃፀም በጠንካራ ክትትልና ድጋፍ እንፈጽማለን ብለዋል፡፡