አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል እየተከናወነ በሚገኛው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ ከ180 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
በ2018 በጀት ዓመት ክልሉን ዘመናዊና ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግ የታቀዱ የኮሪደር ልማት ሥራዎች በ7 ሪጂኦፖሊታን የከተማ አስተዳደሮች እና ከ35 በላይ በሚሆኑ መካከለኛና አነስተኛ ከተሞች ላይ በከፍተኛ ፍጥነትና ስኬት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በመሠረተ ልማት ዘርፍ በበጀት ዓመቱ ከ204 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ለመሥራት ታቅዶ እስካሁን 137 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝም መንገድ ማጠናቀቅ መቻሉን የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ መረጃ አመልክቷል፡፡
በዚህም ከተከናወኑት የሥራ ክፍሎች መካከል 18 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ንጣፍ መንገድ፣ 64 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ እንዲሁም ከ54 ኪሎ ሜትር በላይ የሳይክል መስመር ግንባታ ይገኙበታል።
የከተሞችን ገጽታ ለመቀየርና ማራኪ ለማድረግ በውበት ሥራ ከተያዘው 129 ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ በአሁኑ ወቅት ከ104 ሄክታር በላይ የሚሆነውን ማልማት የተቻለ ሲሆን÷ ከዚህ ውስጥ የመንገድ ዳር አረንጓዴ ልማትንና የመናፈሻ ቦታዎችን ጨምሮ ከ54 ሄክታር በላይ መሬት ለምቷል።
እንዲሁም 12 የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች፣ 20 የውኃ ፋውንቴን፣ 5 የአደባባይ ማስዋብ፣ 5 የልጆች መጫወቻ ቦታዎች፣ 8 የስፖርት ማዘውተሪያዎች እና 299 መለስተኛ ካፌዎች ተገንብተው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል።
ከተሞቹን ይበልጥ ዘመናዊና ደህንነታቸው የተጠበቀ ለማድረግ 6 የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች የተገነቡ ሲሆን÷ የስማርት ፖል ተከላ፣ የደህንነት ካሜራዎች ገጠማ እንዲሁም የመከላከያ ግንብና የጎርፍ መፍሰሻ ቦዮች ግንባታ በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል።
ለፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያ እስካሁን ከ7 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን ÷ለዚህም ከመንግሥት በጀት ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ሲደረግ ቀሪው ከ2 ቢሊየን ብር በላይ በማኅበረሰብ ተሳትፎ የተሸፈነ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ይህ በክልሉ እየተገበረ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ ከመቀየርና ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረግ ባለፈ ከ180 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የቻለ ታላቅ የልማት ምዕራፍ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በከድር መሀመድ