አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለአፋር ክልል ሥነ ምሕዳር መታደስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው አለ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ።
ቢሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በአፋር ክልል ከማህበራዊ እንቅስቃሴ ባለፈ ለክልሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ምላሽ የሚሰጥ የህልውናና የልማት ሥራ ሆኖ መቀጠሉን አመልክቷል፡፡
የክልሉ ስትራቴጂካዊ መልክዓ ምድር በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎች ተጋላጭ ከሆኑ የሀገሪቱ ክፍሎች አንዱ እንደመሆኑ መርሐ ግብሩ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ነው ያለው፡፡
በተለይም በየዓመቱ የሚካሄደው የችግኝ ተከላ የክልሉን አየር ንብረት በማሻሻል፣ የከርሰ ምድር ውሃን በመጠበቅ እና ለእንስሳት መኖ እንዲሁም ለሰው ልጅ የምግብ ዋስትና አስተማማኝ መሰረት እየጣለ መሆኑን አብራርቷል።
መርሐ ግብሩ አፈርን ከመሸርሸር በመታደግ እና የአካባቢውን ሥነ ምህዳር በማደስ በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ የልማት ሥራዎች ተስማሚ አየርን የመፍጠር አቅም አለው፡፡
ባለፉት ዓመታት በአፋር ክልል የተተገበሩት የደን ልማት ተግባራት የክልሉን የደን ሽፋን ለማሳደግ ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም ቢሮው ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
በመርሐ ግብሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸውና እየለሙ የሚገኙ የፍራፍሬና የብዙ ዓመት ተክሎችም የአካባቢውን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ረገድ የጎላ ድርሻ እየወሰዱ መሆኑን አስገንዝቧል።
በአዋሽ ወንዝ ተፋሰስ እና ተያያዥ መስኖ በሚለሙ አካባቢዎች የሚካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ የውሃ ሀብትን ከመጠበቅ ባሻገር በክልሉ የሚገኙ የገጠርና የከተማ ነዋሪዎችን ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የመከላከል አቅም ማጎልበቱ ተጠቅሷል።
በአጠቃላይ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በአፋር ክልል የኢኮኖሚ፣ የአካባቢ እና የማህበራዊ ልማት ድልድይ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡