አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የግሉ ዘርፍ የሚጠበቅበትን ጉልህ ሚና ሊወጣ ይገባል አለ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፡፡
ምክር ቤቱ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በመተባበር “በሀገራዊ የምክክር ሂደት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ” በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የግሉ ዘርፍ በሰላምና መረጋጋት ሂደት ያለው ሚና እና በንግድ ም/ቤቶች የጋራ ርምጃዎችና ትብብር ላይ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ኮሚሽኑ የምክክር አጀንዳ እና የሚወያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ልየታ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
በሂደቱም በሀገርና የሰላም ግንባታ ሂደት የንግዱ ማህበረሰብ ያለውን ሚና በመለየት በሀገራዊ ምክክሩ በቂ ተሳትፎ እንዲኖረው መደረጉን አንስተዋል፡፡
ከተሰበሰቡት አጀንዳዎች መካከል በሀገራዊ ምክክሩ ላይ መቅረብ ያለባቸው አጀንዳዎች ተለይተዋል ነው ያሉት፡፡
የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት አይናለም አባይነህ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዜጎችና በተቋማት መካከል እምነትን ለመገንባት ፈጣን የዲሞክራሲያዊ ሽግግር ሂደት ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱ በምክክር ሂደቱ ላይ መሳተፉ ለኢኮኖሚ ማገገምና ለረጅም ጊዜ ሀገራዊ ልማት ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ አመልክተዋል፡፡
የግሉን ዘርፍ የኢኮኖሚ ጥቅሞችን በመወከል መረጋጋትን በማስፈንና ለሀገራዊ ተግዳሮቶች ተግባራዊ መፍትሄዎችን በማበርከት በምክክሩ ሂደት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አረጋግጠዋል፡፡
በዘመን በየነ