አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በስድስት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች በመጫወት ክብረወሰን ያስመዘገበው ሊዮኔል ሜሲ በ16 ግቦች የዓለም ዋንጫ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትን ክብረ ወሰን ተጋርቷል፡፡
በፈረንጆቹ 2006 በጀርመን ዓለም ዋንጫ በ18 አመቱ ሀገሩን ወክሎ መጫወት የጀመረው የሮዛሪዮው ተወላጅ ሊዮኔል አንድሬስ ሜሲ የዘንድሮውን ጨምሮ በስድስት የዓለም ዋንጫዎች ተሳትፏል፡፡
ትናንት ምሽት አርጀንቲና አልጀሪያን 3 ለ 0 ባሸነፈችበት የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታ ሦስቱንም ግቦች በማስቆጠር ሀትሪክ የሰራው ሜሲ የዓለም መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
ለሀገሩ አርጀንቲና እስካሁን 200 ጨዋታዎችን ያደረገው የ38 አመቱ ኮከብ በጀርመናዊው ሚሮስላቭ ክሎስ ተይዞ የነበረውን የምንጊዜም የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብረወሰን ተጋርቷል፡፡
የ2022ቱ የኳታር ዓለም ዋንጫ አሸናፊው ሜሲ አሁንም የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች መሆኑን ከማስመስከር ባሻገር ሀገሩ በዘንድሮውም ዓለም ዋንጫ ለአሸናፊነት እንድትታጭ አስችሏል፡፡
የዘንድሮውን የዓለም ዋንጫ ጅማሮ በሀትሪክ ያሳመረው ሊዮ ሜሲ በቀጣይ ጨዋታዎች ክብረ ወሰኑን የግሉ የማድረግ ሰፊ እድል አለው፡፡
የ26 አመቱ ፈረንሳዊ ኪሊያን ምባፔ ትናንት ምሽት ሀገሩ ሴኔጋልን ባሸነፈችበት ጨዋታ ያስቆጠራቸውን ሁለት ግቦች ጨምሮ 14 ግቦችን ከመረብ ያሳረፈ ሲሆን፥ ክብረ ወሰኑን የግሉ ለማድረግ ከሜሲ ጋር ተፋጧል፡፡
ሊዮኔል ሜሲ በተጨማሪም በዓለም ዋንጫ ታሪክ በአንድ ጨዋታ ሦስት ግቦችን ያስቆጠረ በእድሜ አንጋፋው ተጫዋች በመሆን ተጨማሪ ክብረ ወሰን የግሉ አድርጓል፡፡
በአቤል ነዋይ