አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በመላ ሀገሪቱ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር እየሰራሁ ነው አለ፡፡
ተቋሙ እንዳስታወቀው ÷ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እና በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል፡፡
በዚህም የኃይል ማመንጫዎችን፣ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን እና የማስፋፊያ መስመሮችን መገንባት ላይ ትኩረት መደረጉን አመልክቷል፡፡
ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ፍላጎት ባለባቸው አካባቢዎች ነባር ግንባታዎችን የማዘመንና ተጨማሪ የማስፋፊያ ሥራ በመከወን ላይ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በማስፋፊያ ሥራዎቹ የደብረ ማርቆስ እና ባህር ዳር ኮሪደር እንደሚገኙበት ነው የተገለጸው፡፡
አሁን ላይ አፈጻጸሙ 55 በመቶ የደረሰው የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ሲጠናቀቅ የእንጅባራ ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ እንደሚጀመር ተገልጿል።
የእንጅባራ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ከዓለም ባንክ በተገኘ 19 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ብድር የሚገነባ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በፍቅርተ ከበደ