የሀገር ውስጥ ዜና

በጉባኤው 4 ሺህ ተወካዮችን ለመቀበል ዝግጅት ተደርጓል – መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)

By Hailemaryam Tegegn

June 17, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሐምሌ 8/2018 ዓ.ም ጀምሮ በሚካሄደው ታሪካዊ ጉባኤ 4 ሺህ ተወካዮችን ለመቀበል ዝግጅት ተደርጓል አለ፡፡

ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፥ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መግባባትን ለመፍጠር የተጀመረው ሀገራዊ የምክክር ሂደት በርካታ ፈታኝ መንገዶችን አልፎ ወሳኙ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

ሂደቱን ፍፁም አካታችና አሳታፊ ለማድረግ የታጠቁ ኃይሎችን፣ ተፈናቃዮችን እና ከሀገር ውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ለማካተት ሰፊ ጥረት መደረጉን አብራርተዋል።

ምክክር በፍላጎት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ወደ ዋናው ጉባኤ በር ላይ እስከሚደረስ ድረስ አሁንም አጀንዳዎችን የመቀበል ሥራው ክፍት መሆኑን ጠቁመዋል።

ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚጀምረው ታሪካዊ ጉባኤ ከየአካባቢው የተወከሉ 4 ሺህ ተሳታፊዎች አዲስ አበባ እንደሚገቡ የገለጹት ኮሚሽነሩ፥ ለዚህም ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

ጉባኤው በተከባበረና በተደማመጠ መንፈስ ተወካዮቹ ችግሮቻቸውን እየተጋሩ ለመፍትሔው የሚመክሩበት እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

ከጉባኤው በኋላ የሚቀመጡ ምክረ ሀሳቦች በተግባር ላይ መዋላቸውን ኮሚሽኑ በቅርበት ክትትል እንደሚያደርግ ጠቁመው፥ በጉባኤው ማግስት በሀገሪቱ የመነጋገርና የመመካከር ባህል እንደሚዳብር ነው የገለጹት፡፡

ዋና ኮሚሽነር አክለውም ምክክር ሁሉንም አካል አሸናፊ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በቅድስት ዘውዱ