አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የኢራን ፕሬዚዳንት መሱድ ፔዜሽኪያን ጦርነቱን ማስቆም የሚያስችለውን የመጀመሪያ ደረጃ የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ የሆርሙዝ ወሽመጥን በድጋሚ መክፈት፣ ለኢራን መልሶ ግንባታ የሚውል የ300 ቢሊየን ዶላር ዕቅድን እና አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለቻቸውን ማዕቀቦች ማንሳትን ያካተተ ነው፡፡
እንዲሁም የኢራን የኒውክሌር መርሐ ግብር ጉዳይ ሊራዘም በሚችል የ60 ቀናት የጊዜ ገደብ ውስጥ ድርድር የሚካሄድበት እንደሚሆን ተመላክቷል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ፥ የቀረበውን የሰላም ዕቅድ በመደገፍ ስምምነቱ ሊከሰት የነበረውን “የኢኮኖሚ ጥፋት” የሚያስቀር መሆኑን ገልጸዋል።
በአንጻሩ የመጨረሻ ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ አሜሪካ ኢራንን በቦምብ እንደምትደበድብ ነው ያስጠነቀቁት፡፡
ለኢራን የተመደበውን የ300 ቢሊየን ዶላር ፈንድ በተመለከተ ደግሞ በአሜሪካ የሚከፈል ሳይሆን የኢራን የራሷ የታገደ ሃብት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢራኑ ፕሬዚዳንት መሱድ ፔዜሽኪያን ረቡዕ ዕለት ሰነዱን መፈረማቸውን አረጋግጠዋል።
የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔና ዋናው ተደራዳሪ መሀመድ ባገር ጋሊባፍ ለሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፥ በተፈረመው ስምምነት ላይ የሆርሙዝ ወሽመጥ ለ60 ቀናት ክፍት እንዲሆን ተናግረዋል፡፡
ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም ግንባሮች ላይ የሚደረጉ ወታደራዊ ዘመቻዎች እንዲቆሙም አብራርተዋል፡፡
አሜሪካ፣ እስራኤል እና ኢራን በጀመሩት ጦርነት የኢራን የበላይ መሪ አያቶላ አሊ ኻሚኒ እና ከፍተኛ የወታደራዊ መኮንኖች መገደላቸው ይታወሳል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ግጭቱ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ በመምጣቱ እና በተለይም ኢራን ቁልፍ የንግድ መስመር የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዝጋቷ ምክንያት የነዳጅ ዋጋ እንዲንርና የዋጋ ንረት እንዲባባስ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡
በዮናስ ጌትነት