አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ የዲፕሎማሲ ድሎች የኢትዮጵያን ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ወደ ላቀ ከፍታ ማሸጋገር ችለዋል፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነቷ የምትታወቀው የቀጣናዊ አጀንዳዎች ምንጭ እና የመፍትሔ አካል በመሆን ነው።
በዚህ ተለዋዋጭ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ በሳል፣ በስትራቴጂ የሚመራና ብሔራዊ ጥቅም ላይ ያነጣጠረ የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ሥራዎችን የኢትዮጵያ መንግሥት አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
የለውጡ መንግሥት የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ዋነኛ መለኪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ነው፤ ኢትዮጵያ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የራሷን የሉዓላዊነትና የልማት ፍላጎት ማዕከል ያደረገ የውጭ ግንኙነት መርህን እየተከተለች ትገኛለች፡፡
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ያጋጠሙ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን በብቃት በመቋቋም እና የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነቶችን በማጠናከር እንደ ኢትዮጵያና ብሪክስ አባልነት ያሉ የሀገራዊ ክብር ማሳያ የሆኑ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ ጥምረትን መቀላቀሏ በዓለም አቀፍ ተቋማት ምስረታ እና በአባልነት ያላት ታሪካዊ ሚና እያደገ መምጣቱን ያሳያል፡፡
ይህ ውጤት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነትና የውሳኔ ሰጪነት አቅም በተግባር ያረጋገጠ ነው።
ቅድሚያ ለጎረቤት የሚለው መርህ ከቃላት ባለፈ በተግባራዊ ዲፕሎማሲ በመተርጎሙ ቀጣናዊ ግንኙነት ከጥርጣሬ ወጥቶ ወደ ጽኑ ስልታዊ አጋርነት ተሸጋግሯል።
ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የትስስር ማዕከል በመሆን በታዳሽ ኃይል ፣ በመንገድ፣ በመጠጥ ውሃ እና በባቡር መሠረተ ልማቶች የቀጣናውን ሀገራት ዕጣ ፈንታ ከራሷ ጋር አስተሳስራለች።
ይህ የጋራ ዕድገት ስትራቴጂ ኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ምሰሶ ብቻ ሳይሆን የማይበገርና መሪ ቀጣናዊ ኃይል እንድትሆን አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡
በዓለም ዲፕሎማሲያዊ መድረኮች ተፅዕኖዋ እየጎላ የመጣው ኢትዮጵያ አሁንም የፓን አፍሪካኒዝም ማማና የፅናት ተምሳሌት መሆኗን ለዓለም በድጋሚ ያረጋገጠ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ያላትን ተሳትፎ በማጠናከር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴዋን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡
ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ በርካታ ሀገራት ተቀራርበው በመምከርና በመደራደር ድንበር ተሻጋሪ ችግሮችን ለመፍታትና የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል ወሳኝ መድረክ ነው።
ኢትዮጵያ በቀጣናዊ ትብብር እና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ረጅም ታሪክና የማይቋረጥ አሻራ ያላት ሀገር ስትሆን ሁልጊዜም በፍትሃዊነትና በእኩልነት መርህ ታምናለች፡፡
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ በአንድ ወገን ላይ ብቻ ከመወሰን ይልቅ አጋርነትን በማስፋት ላይ ያተኮረ ሲሆን÷ ይህም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ እየተተገበረ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት እና በሌሎችም መድረኮች ታዳጊ ሀገራት በዓለም አቀፍ የንግድ፣ የገንዘብ ተቋማት እና የአየር ንብረት ለውጥ ድርድሮች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትሟገታለች።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን እና ሌሎች በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ መሆኗ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ጋር ያላትን ግንኙነትና የጋራ ተጠቃሚነት በቀላሉ እንድታስተሳስር ትልቅ አጋጣሚ ፈጥሮላታል።
በወንድማገኝ ጸጋዬ