አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለሀገራዊ የምክክር ጉባዔ የሚያደርጋቸው የቅድመ ዝግጅ ሥራዎችን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በዛሬው ዕለትም የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ አመካካሪዎች ሁለተኛ ዙር ሥልጠናን በአዲስ አበባ አስጀምሯል፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ (ፕ/ር) በዚህ ወቅት÷ የሀገራዊ ምክክር ሒደት ከስሜታዊነት ወደ ምክንያታዊነትና መግባባት ደረጃ እንዲደርስ የአመካካሪዎች ሚና የላቀ ነው ብለዋል፡፡
የሥልጠናው ዓላማ አመካካሪዎች አካታችና ገለልተኛ የምክክር ሒደት እንዲያሳልጡ የሚያስችላቸውን ዓለምአቀፍ ዕውቀትና ክህሎት እንዲጨብጡ ለማድረግ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም አስተባባሪ ሳሙኤል ዶኤ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያዊያን በተስፋ የሚጠብቁትን የሀገራዊ ምክር ውጤት እውን ለማድረግ ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አድንቀዋል፡፡
አመካካሪዎች የሀገራዊ ምክክር ጉባዔው መርሕን ጠብቆ እንዲከናወን የወሰዱትን ሥልጠና ተጠቅመው ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙ የአጋር ሀገራት አምባሳደሮችም ይህንን ታሪካዊ የምክክር ምዕራፍ ፍሬያማ ለማድረግ በፋይናንስ፣ በዲፕሎማሲ እና በቴክኒክ እያደረጉ ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
ሥልጠናው ለሚቀጥሉት ሰባት ቀናት የሚቆይ መሆኑንም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡