የሀገር ውስጥ ዜና

በፍትሐዊነት መጠቀምን መርሕ ያደረገ ዲፕሎማሲ

By Adimasu Aragawu

June 18, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዲፕሎማሲ ብሔራዊ ጥቅም እና ሀገራዊ ክብርን ከፍ አድርጎ ማሳየት የሚቻልበት ጥበብ ነው።

የዲፕሎማሲ ስራ እርዳታ እና ብድር ለማግኘት ሲባል የሚከወን ሳይሆን የመደራደር አቅምን ከፍ በማድረግ ያለንን የማሳየት አቅም እና ተደማጭነትን መፍጠር መሆን ይጠበቅበታል።

ስለሆነም ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኃያላኑ ሀገራት ፍላጎት ከመፍሰስ ይልቅ የመሪዎችን ቀልብ ወደመሳብ ተሸጋግራለች። በዚህም የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እሳቤ የዓለም ኃያላን ሀገራት መሪዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ማድረግ ተችሏል።

በያዝነው ክፍለ ዘመን የዓለም ሀገራት እድገትና ብልጽግና በትብብር፣ በአጋርነት እና በጋራ ጥረት ላይ እየተመሰረተ መጥቷል። በዚሁም ሀገራት በተናጥል ከመስራት ይልቅ የጋራ ጥቅምን በሚያጎለብቱ ግንኙነቶች ላይ ትኩረት እያደረጉ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያም ይህንን እውነታ በመገንዘብ ከሁሉም ጋር በእኩልነት፣ በመከባበር እና በጋራ ጥቅም ላይ በተመሰረተ መልኩ ለመስራት በሯን ክፍት አድርጋለች።

ኢትዮጵያ ሰፊ የገበያ እድል፣ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች፣ ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች እና አምራች የሰው ኃይል ያላት ሀገር እንደመሆኗ መጠን የኃያላን ሀገራት ትኩረት ወደመሆን ተሸጋግራለች።

በዚህ ወቅት ዲፕሎማሲው የሚፈልጋቸው ጉዳዮች የራስን አቅም ከፍ ማድረግ፣ የመደራደር ችሎታን ማሳደግ፣ ያለንን ሀብት በአግባቡ ማሳወቅ እና ለራሳችን የምንሰጠውን ቦታ ማወቅ የሚሉት መሆን ይኖርባቸዋል። ኢትዮጵያ በዚህ አውድ እየተጓዘች ትገኛለች።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ያሏት አቅሞች ለውጭ ኢንቨስተሮች፣ ለልማት አጋሮች እና ለንግድ ተቋማት ሰፊ እድሎችን እንደሚፈጥሩ በማስተዋወቅ የሚታይ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት አስመዝግባለች።

ሀገሪቱ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በኢነርጂ እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፎች ያላትን እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ እድገት ለመቀየር ከተለያዩ አጋሮች ጋር እየሰራችም ትገኛለች፤ ወደፊትም በሯን ክፍት አድርጋ ትቀጥላለች።

የኢትዮጵያ የትብብር አቅጣጫ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ነው። ሀገሪቱ የራሷን ጥቅም ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ከአጋሮቿ ጋር ዘላቂ ግንኙነት በመገንባት የጋራ እድገትን ለማምጣት ትሰራለች። ይህ አካሄድም እጅ ጠምዝዘው የሚፈልጉትን ለማድረግ ለሚሹ ኃይሎች የማይበገር አጥር ሆኗል።

በብርሃኑ አበራ