የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ 2ኛውን የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ እንድታስተናግድ ተመረጠች

By sosina alemayehu

June 18, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ ገቨርናንስ ማዕከል ዋና ዓመታዊ መድረክ የሆነውን ሁለተኛውን የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ እንድታስተናግድ ተመርጣለች።

ጉባዔው በፈረንጆቹ ጥቅምት 2026 መገባደጃ ላይ በአዲስ አበባ “ለዕድገት መምራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአፍሪካ ኢኮኖሚ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ቀራፂዎች” በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።

ጉባዔው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት፣ ተቋማትን ለማጠናከር እና በአህጉሪቱ ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን ለማምጣት ያላቸውን ወሳኝ ሚና የሚያጎላ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ለ2026ቱ አህጉራዊ ጉባዔ የሚደረገውን ዝግጅት በተመለከተ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ከአፍሪካ ገቨርናንስ ማዕከል የሥራ አስፈጻሚ ም/ቤት ሰብሳቢ ቤኔዲክታ ላሲን ጋር ተወያይተዋል፡፡

አቶ አደም ፋራህ በውይይቱ ወቅት÷ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ገንቢ ውይይት እንዲኖር የሚያስችሉ አፍሪካውያን እራሳቸው የሚመሯቸው መድረኮች መኖራቸው ያለውን ጠቀሜታ አንስተዋል።

ሁለቱ ወገኖች የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአህጉሪቱ ለሚመጣው ሁሉን አቀፍ ሽግግር ቁልፍ አንቀሳቃሽ ኃይል ለማድረግ የተቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት በጋራ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

በዚህ ጉባዔ ላይ የሀገራት መሪዎች፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ የፖሊሲ አውጪዎች፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣ የባለሃብቶች ተወካዮች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ምሁራን እና የልማት አጋሮች እንደሚሳተፉ ተመላክቷል፡፡