አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የክረምት በጎ ባህሎቻችንን ወደ ላቀ መገለጫነት እናሻግራለን አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት።
አገልግሎቱ ጉዳዩን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል።
ኢትዮጵያውያን ባለፉት የለውጥ ዓመታት ክረምት በመጣ ቊጥር የምንከውናቸው ሁለት አንኳር ባህሎችን እየገነባን መጥተናል፤ ኢትዮጵያን አረንጓዴ ማልበስ እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፡፡
ኢትዮጵያ የደን ሀብቷ እየተመናመነ፣ የዐፈር መሸርሸር እና ድርቅ ተጋላጭነቷ እየጨመረ መምጣቱን በመገንዘብ መንግሥት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን በሚሊዮን ችግኞች ተከላ በማብሰር ከጥቂት ዓመታት በፊት ጀምሯል፡፡
ኢትዮጵያውያንም ይህንን በጎ ጅምር እና የመዳረሻ ትልም በላቀ ደረጃ በመገንዘብና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩን በተነሣሽነት በመተግበር ዓለምን ያስደመሙ ስኬቶችን አስመዝግበናል፡፡ በሂደቱ የምግብ፣ የደን እና የውበት ችግኞችን በመትከል ዐሻራችን እያኖርን ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ ባህላችንን በእጅጉ አጎልብተናል፡፡
በየዓመቱ በርካታ ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የዓለም ሕዝብን ከአምስት እጥፍ የሚበልጥ ከ48 ቢሊዮን ላይ ችግኞች ተክለናል፤ በዚህም የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ትርጒም ባለዉ መጠን አሳድገናል፤ ለምግብ ሉዓላዊነታችን መሠረት መጣል ጀምረናል፤ የፍራፍሬ የወጪ ንግዳችን አሳድገናል።
ከሁለት ዓመታት በፊት ይፋ በተደረገ የጥናት ውጤት መሠረት የደን ሽፋናችን እጅግ ከተመናመነበት በከፍተኛ ፍጥነት አገግሞ ወደ 23.6% አድጓል፡፡
በልዩ ኹኔታ የኢትዮጵያውያንን የተቀናጀ እና የተሰናሰነ ተነሣሽነት በሚጠይቁ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሮችም የዓለምን ትኩረት በሳበ መልኩ ሚሊዮኖች በአንድ ጀምበር እየወጣን በመትከል የራሳችንን ክብረ ወሰን በራሳችን ደጋግመን እያሻሻልን መጥተናል፡፡
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተከልናቸው የምግብ፣ የደን እና የውበት ችግኞች የኢትዮጵያን ኹለንተና የሚቀይሩ፣ የምግብ ሉዓላዊነታችንን የሚያረጋግጡ፤ የአበባ እና ፍራፍሬ ወጪ ንግዳችንን ዕድገት እየለወጡ ያሉ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም ዐቅም ያጎለበቱ ናቸው፡፡
በመኾኑም ይህ ክረምት በመጣ ቊጥር በንቅናቄ የሚከናወን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ባህል የበለጠ እንዲጠናከርና እንዲጎለብት በትጋት መሥራታችንን እንቀጥላለን፤ ኢትዮጵያን አረንጓዴ በማልበስ ንጹሕ አየር ለዓለም እናበረክታለን፡፡ ዘንድሮም የራሳችንን ክብረ ወሰን በራሳችን የላቀ የሚሊዮኖች ተሳትፎ በማሻሻል ጭምር ከ8 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን እንተክላለን፡፡
የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ሌላኛዉ ዐዲስ እያደገ የመጣ ልምምዳችን ነው፡፡ ወጣቶች ዕውቀታቸዉን እና ከትምህርት የተረፈ ጊዜያቸውን፣ ባለሀብቶች ደግሞ ሀብታቸውን በማዋጣት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ ዐቅመ ደካማ ወገኖችን ቤት በመገንባት፣ ማዕድ በማጋራት እጅግ የተዋጣለት ልምምድ አዳብረዋል፡፡
የመንግሥት ተቋማትም በቁጠባ ከሚጠቀሙት ሀብታቸው በማዋጣት ይህንን የበጎ አድራጎት ልምድ የማስፋት እና ወደ ላቀ ባህል ደረጃ የማሳደግ ኃላፊነትን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡
በለውጡ ዓመታት በአዲስ አበባ እና በክልሎች የበርካታ ዐቅመ ደካሞች ቤት ታድሷል፤ በዐዲስ መልክ ተገንብቷል፤ ሕይወታቸዉ እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡ በከተሞች የተጀመረዉ የኮሪደር ልማት ወደ ገጠር ተስፋፍቷል። ኢትዮጵያውያን ችግሮቻችንን ተጋግዞ የመፍታት ባህል እያዳበርን መጥተናል፡፡
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደየአካባቢያቸው በመሄድ እና በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ታናናሾቻቸውን እያስተማሩ፣ እንደ ደም ልገሳ ያሉ ሕይወት አዳኝ ተግባራትን እያስተባበሩ፣ ዐቅመ ደካሞችን በማገዝ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው፡፡
በመኾኑም በየክረምቱ በበጎ ልምድነት እያሳደግናቸው የመጡ የአረንጓዴ ዐሻራ እና የበጎ ፈቃድ ሥራዎች የበለጠ ሀገራዊ መገለጫችንና ባህላችን እንዲኾኑ ዘንድሮም ካለፉት ዓመታት የላቀ ተሳትፎ የሚጠይቅ ዕቅድ ተዘጋጅቷል፤ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።
በተደመረ ዐቅማችን የኢትዮጵያን ዕቅድ በሚገባ ለማሳካት ቅድመ ዝግጅት ጨርሰን ወደ ትግበራ ገብተናል። ድላችንን በጋራ የምናበስርም ይኾናል።
የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ግንቦት 12 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ