አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ተግዳሮት ናቸው ከሚባሉት ውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግር እና ብልሹ አሰራሮች ይጠቀሳሉ፡፡
መሰል ችግሮችን ለመፍታትም በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ዜጎች ላይ ምሬት የሚፈጥሩ አሰራሮችን ፈትሾ ማስተካከል ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያም በተለያዩ ዘርፎች የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና ብልሹ አሰራሮችን ለመፍታት በትኩረትና በቁርጠኝነት እየሰራች ትገኛለች፡፡
ለዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በተለያዩ ከተሞች መተግበር የጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡
በኢትዮጵያ በተሟላ ማዕድ የሚወክለው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአንድ ጣራ ስር የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶችን በማጣመር የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሚሰጥ አገልግሎት ነው።
የኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር ትልቅ ርምጃ የሆነው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግሥት ቀልጣፋ፣ ተዓማኒና ቀጣይነት ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርም ማሳያ መሆኑን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ማዕከሉ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን በአንድ ላይ አቀናጅቶ የያዘ በመሆኑ ዜጎች የተሳለጠ እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ነው፡፡
የአሰራር ሥርዓቱ ዜጎች የተሟላ የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም በቀላሉ የተለያዩ የፌዴራል ተቋማት አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እንዲሁም እንግልትንና አላስፈላጊ ወጪን በማስቀረት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎትን ተዳራሽ ማድረግ ያስችላል፡፡
መሶብ ባለጉዳዮች ወደ ተለያዩ ቢሮዎች የሚያደርጉትን ምልልስ፣ ረጅም የወረፋ ጥበቃ እና ከወረቀት ጋር ተዛማጅ የሆኑ ሥራዎችን የሚያስቀር ሁነኛ መፍትሄ መሆኑንም ማዕከላቱ እየሰጡት ከሚገኙ ስሉጥ አገልግሎት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
መሶብ አንድ ማዕከል የሕዝብን የአገልግሎት ፍላጎት ያማከለና ሁሉም ዜጎች በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ በአክብሮትና በኃላፊነት መንፈስ የሚገለገሉበት መሆኑ ዘመኑን የዋጀ ያደርገዋል፡፡
በተለይም ለአካል ጉዳተኞችና ለአቅመ ደካሞች ልዩ ትኩረትና ቅድሚያ መስጠቱ ቀደም ሲል ይገጥማቸው የነበረውን እንግልት ለመቅረፍ አስችሏል፡፡
መሶብ ዘመኑን የዋጀና የተለያየ አገልግሎትን በአንድ ጣሪያ ሥር ከመስጠቱ ባለፈ ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል አሰራር ያለው መሆኑም ልዩ ያደርገዋል፡፡
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መንግሥት ለሰው ተኮር አገልግሎት የሰጠው ትኩረት ማረጋገጫ ሲሆን÷ በሀገሪቱ የአገልግሎት አሰጣጥም እንደ ታሪክ እጥፋት የሚቆጠር ትልቅ ስራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በሁሉም አካባቢዎች በማስፋት በዘመናዊ አገልግሎት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የምታከናውነው ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
አሁን ላይ በአዲስ አበባ ብቻ 9 መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ሥራ የጀመሩ ሲሆን ÷ በክልሎችም በበርካታ ከተሞች ማዕከላቱን የማስፋፋት ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡
ለአብነትም አዳማ ፣ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር፣ አርባ ምንጭ፣ ሀዋሳ፣ ነቀምቴ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ዲላ፣ ደሴ እና ሌሎች ከተሞች ላይ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ሥራ ጀምረዋል፡፡
በቀጣይም ማዕከሉን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ የዜጎችን እንግልትና አላስፈላጊ ወጪ የሚያስቀር ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በቅንጅት መስራት ይገባል፡፡
በመላኩ ገድፍ