ዓለምአቀፋዊ ዜና

ተጠባቂው የአሜሪካ እና ኢራን የሰላም ውይይት ተራዘመ

By Hailemaryam Tegegn

June 19, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ እና ኢራን መካከል በዛሬው ዕለት በስዊዘርላንድ ሊካሄድ የነበረው የሰላም ውይይት ተራዝሟል፡፡

አሜሪካ እና ኢራን ከሳምንታት ውይይት በኋላ ባለ 14 ነጥብ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ ለመጨረሻው ስምምነት በዝርዝር ጉዳዮች ላይ የሚደረገው ድርድር ዛሬ እንደሚጀመር ተገልጾ እንደነበር ይታወሳል።

ይሁን እንጂ የስዊዘርላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፥ አሜሪካ፣ ኢራን፣ ኳታር እና ፓኪስታንን በማሳተፍ ለማካሄድ ታቅዶ የነበረው ውይይት ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል ብሏል።

ሚኒስቴሩ በመግለጫው ድርድሩ ለምን እንደተራዘመና በቀጣይ መቼ እንደሚካሄድ አልገለጸም፡፡

ከመግለጫው ቀደም ብሎ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ለድርድሩ ወደ ስዊዘርላንድ የሚያደርጉትን ጉዞ መሰረዛቸው ተገልጾ ነበር።

ይህም ምናልባት በአሜሪካ እና ኢራን መካከል በሚጠበቀው ዘላቂ እርቅ ላይ ተጽዕኖ እንዳይኖረው ተሰግቷል።

በኢራን ባለስልጣናት በኩል በጉዳዩ ላይ እስካሁን የተሰጠ ይፋዊ ምላሽ አለመኖሩን ሮይተርስ ዘግቧል።

በብርሃኑ አበራ