አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ2026/27 የውድድር ዘመን የጨዋታ መርሐ ግብር ይፋ ተደርጓል፡፡
ሻምፒዮኑ አርሰናል በሜዳው ኢምሬትስ ከአዲስ አዳጊው ኮቬንትሪ ሲቲ ጋር የሊጉን የመክፈቻ ጨዋታውን ያደርጋል።
በአዲሱ አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካ የሚመራው ማንችስተር ሲቲ በሜዳው ከ በርንማውዝ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል፡፡
በአሰልጣኝ ማይክል ካሪክ የሚመራው ማንቼስተር ዩናይትድ በበኩሉ ወደ ሊጉ ካደገው ሃል ሲቲ ጋር በመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታው ይገናኛል፡፡
አንዶኒ ኢራኦላን በኋላፊነት የሾመው ሊቨርፑል ከኒውካስል ዩናይትድ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
ከአውሮፓ ውድድሮች ውጪ ሆኖ የውድድር ዓመቱን ያጠናቀቀው ቼልሲ በመጀመሪያ ሳምንት ከፉልሀም ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
ሌላኛው ወደ ሊጉ ያደገው ኢፕስዊች ታውን የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታውን ከሰንደርላንድ ጋር የሚያደርግ ይሆናል፡፡
የወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን አርሰናል በ3ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር በሜዳው ቼልሲን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡
በሊጉ ከሚጠበቁ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው የአርሰናል እና ማንቼስተር ዩናይትድ ጨዋታ በ16ኛ ሳምንት በኢምሬትስ ስታዲየም ይካሄዳል፡፡
ተጠባቂው የማንቼስተር ደርቢ ጨዋታ በ4ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር በኦልድትራፎርድ ይደርጋል፡፡
የላንክሻር ደርቢ ጨዋታ ደግሞ በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም በ11ኛ ሳምንት የሚካሄድ ይሆናል፡፡
በመርሐ ግብሩ መሰረት አዲሱ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን ነሐሴ 15 ቀን 2018 ዓ.ም የሚጀመር ይሆናል፡፡