ፋና ስብስብ

ታዋቂው የሙዚቃ ማናጀር አቶ አዲሱ ገሰሰ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

By Yonas Getnet

June 19, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም አቀፍ እውቅናን ያገኘው እውቁ የሙዚቃ ማናጀር አቶ አዲሱ ገሰሰ ባደረበት ሕመም በአሜሪካ ሀገር በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡

አቶ አዲሱ ገሰሰ ወደ ሙዚቃ ማናጀርነት ከማምራቱ በፊት በዲሲፕሊን አንፆኛል በሚሉት ዝነኛው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በግራንድ ቴክኒሻንነት ለአንድ ዓመት አገልግሏል።

ወደ አሜሪካ ቺካጎ በማቅናት ራንቱል ኤርፎርስ ቤዝ እና ቴክሳስ ላክላንድ ኤርፎርስ ቤዝ ትምህርቱን ተከታትሎም ተመርቋል፡፡

በሃሮልድ ዋሺንግተን ዩኒቨርሲቲ በሉፕ ኮሌጅ ሜካኒካል ኢንጅነሪንግ ትምህርቱን የተከታተለው አቶ አዲሱ÷ በኖርዝ ኢስተርን ኢሊኖይስ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የማኔጅመንት ትምህርቱን አጠናቅቋል፡፡

አቶ አዲሱ ገሰሰ ይማርበት በነበረው ዩኒቨርሲቲ ስር የጥቁር ታሪክ ወር ተብሎ በየዓመቱ የካቲት ወር ላይ በሚቀርበው ዝግጅት ላይ ወንድሞቹ ዘለቀ ገሰሰ፣ ሙሉጌታ ገሰሰ እና ጓደኞቹ በዳሎል ባንድ ስር ሙዚቃ እንዲያቀርቡ በማስቻል ነበር የማኔጅመንቱን ሥራ በመስራት የሙዚቃ ሕይወት ጉዞውን አንድ ብሎ የጀመረው፡፡

በመቀጠልም በአሜሪካ ዋሺንግተንና ሎስ አንጀለስ ከተሞች ለኢትዮጵያውያን የመጀመሪያውን የሙዚቃ መድረክ በዳሎል ባንድ አማካኝነት መስራት ችሏል፡፡

አቶ አዲሱ ገሰሰ የማርሌን ቤተሰብ ከነሃብት ንብረቱ በሚያስተዳድሩበት ጊዜ ዘመን አይሽሬውን ኤክሶደስ ሌጀንድ አልበም ከአይስ ላንድ ሪከርዲንግ ጋር እንዲሰራ አድርጓል።

ዚጊን ከጃማይካ የነ ዘለቀን ዳሎል ባንድ ከሺካጎ ወደ ኒዮርክ በማምጣት ካጣመሩ በኋላ በአሜሪካ ምድር ቁጥር አንድ አልበም የሆነውን ኮንሺየስ ፓርቲን ማኔጅ በማድረግ ዚጊ ማርሌ የአሜሪካንን ትልቁን ግራሚ አዋርድ ሽልማት ሲያገኝ የኢትዮጵያ ዳሎል ባንድ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ባንድ የግራሚ ሽልማቱን እንዲወስዱ አስችሏል፡፡

ከወንድሙ አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ ጋር በመሆን የቦብ ማርሊ 60 ዓመት የልደት በዓሉን ምክንያት በማድረግ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ዝግጅት ኢትዮጵያን መዳረሻ በማድረግ በ1997 ዓ.ም መስቀል አደባባይ የተካሄደውን የሙዚቃ ፌስቲቫል ስኬታማ እንዲሆን አድርጓል፡፡

አቶ አዲሱ ገሰሰ በሙዚቃ ማኔጅመንት ስራቸውም ለእጅጋየው ሽባባው (ጂጂ)፣ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) እና ለሌሎች የማኔጅመት ሥራውን በመያዝ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡

ጃኖ ባንድን በመመስረት እና ለፍሬ እንዲበቁ የአቶ አዲስ ገሰሰ ድጋፍ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዝ ነበር፡፡ አቶ አዲስ ጃናናይት የተባለ ተሰጥዖ ያላቸውን ሴቶች የያዘም ባንድ መስርቶ ለመጓዝ ያደረገው ጥረት የሚጠቀስ ነው፡፡

አቶ አዲሱ ገሰሰ ከሀገራችን ውጪ የማርሌ ቤተሰብ እና ሌሎች በርካታ ሙዚቀኞችን በማስተዳደር በዓለም አቀፍ ደረጃ የብዙዎችን የሙዚቃ ስራ መስመር አስይዟል።

በበጎ ስራ ተግባሩ በግል ከደገፋቸው ግለሰቦች በተጨማሪ በኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ የተፈጠሩ ሰብዓዊ ችግሮችን ለመድረስ ያደረገው አስተዋፅኦ የሚጠቀስ ነው።

በዋናነት ከወንድሙ ዘለቀ ገሰሰ ጋር በመሆን በተለያዩ ገጠራማ አካባቢዎች 30 ትምህርት ቤቶችን በማሰራት የበጎ ተግባር ሥራ ማከናወኑ ይታወቃል፡፡

በ73 ዓመቱ ሰኔ 9 ቀን 2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው አቶ አዲሱ ገሰሰ÷ ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነበር፡፡

የአቶ አዲሱ የአስክሬን ሽኝትና ሥርዓተ ቀብር አፈጻጸም በተመለከተም በቅርቡ እንደሚገለጽ ከቤተሰቦቻቸው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በለምለም ዮሐንስ