የሀገር ውስጥ ዜና

ቡድኑ የትግራይን ሕዝብ ጥቅም ያስቀደመበት አንድም ጊዜ የለም – አታክልቲ ኃ/ሥላሴ

By Mikias Ayele

June 19, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀድሞው ህወሓት የሕዝብን ጥቅም ያስቀደመበት አንድም ጊዜ የለም አሉ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የቀድሞ የመቀሌ ከተማ ከንቲባ አታክልቲ ኃ/ሥላሴ፡፡

አቶ አታክልቲ ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ቡድኑን የሚመሩት ግለሰቦች ለኢትዮጵያም ሆነ ለትግራይ ክልል ሕዝብ ጥቅም ሳይሆን ለግል ጥቅማቸው ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ቡድኑ በክልሉ የዜጎችን ሀሳብ የመግለጽ ነጻነት የሚከለክልና ምንም ዓይነት ጉዳዮችን በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን የሚነጥቅ አዋጅ በማውጣት አፋኝ ተግባር እየፈጸመ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

ይህ አፋኝ አዋጅ የክልሉ ሕዝብ የቡድኑን የጦርነት እንቅስቃሴ ከተቃወመና ያለውን ነገር ለጦርነት ዝግጅት የማያውል ከሆነ ወንጀል አድርጎ የሚወስድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ቡድኑ የክልሉ ነዋሪዎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስን፣ መደራጀትን፣ መብት መጠየቅን፣ የግል ሀብትን ማስተዳደር እንዲሁም ለሰላምና ለፍትህ መቆምን ጭምር በወንጀልነት የፈረጀ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡

የቀድሞው ህወሓት የሚፈጽመው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በአሁኑ ወቅት የትግራይን ሕዝብ ከየትኛውም ጊዜ በላይ አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ አድርጓል ነው ያሉት፡፡

ቡድኑ ለትግራይ ሕዝብ እታገላለሁ ቢልም በተጨባጭ የትኛውን የክልሉን ሕዝብ ጥያቄ ይዞ እንደተነሳና የትኛውን ጥያቄስ መለሰ የሚለው ጉዳይ ቢፈተሽ ያመጣው ለውጥ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

የቡድኑ አመራሮች ለራሳቸውን ፍላጎት እንጂ ለሕዝብ ጥቅም እንደማይታገሉ ገልጸው፥ ቡድኑ በአሁኑ ጊዜ በሚያወጣቸው ተከታታይ መግለጫዎች አንድም ቀን ሕዝብን ያስቀደመበት ጊዜ እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡

በቴዎድሮስ ሳህለ