የሀገር ውስጥ ዜና

መንግሥት ሁሉንም አገልግሎቶች ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመቀየር እየተጋ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Yonas Getnet

June 20, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት ሁሉንም አገልግሎቶች ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመቀየር እየተጋ ነው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

ዲጂታል ለልህቀት በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀው ጉባዔ የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት የሞባይል መተግበሪያን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ መርቀው ሥራ አስጀመረዋል።

ይህንን አስመልክቶ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማሕበራዊ የትስስር ገጻቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕት እንዳሉት÷ የኢትዮጵያ የመሶብ ዲጂታል ማዕከል በተጀመረ በአንድ ዓመት ጊዜ ወስጥ ቁጥሩን 70 ማድረስ ተችሏል።

በተጨማሪም የተንቀሳቃሽ አገልግሎቶች መጀመራቸውን ገልጸው÷ በኢትዮጵያ በሙስና የተተበተበ፣ ኋላ ቀር፣ ፍጥነት እና ጥራት የጎደለው እንዲሁም ዜጎችን ለእንግልት የዳረገ የአገልግሎት አሰጣጥ ታሪክ ከመሰረቱ እየተቀየረ እንደሆነ ጠቁመዋል።

አሁን ላይ ይህንን ችግር በመቅረፍ ከስር መሰረቱ የሚቀይር የኢትዮጵያ የመሶብ ዲጂታል አገልግሎትን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የማስፋፋት ሥራ በተጀመረ በአንድ አመት ጊዜ ወስጥ ቁጥሩን ወደ 70 ማድረስ መቻል እጅግ የሚያስደንቅ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይ በጀት ዓመት ውስጥ መንግሥት ሁሉንም አገልግሎቶች ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመቀየር እየተጋ መሆኑንም ነው ከንቲባዋ የገለጹት።