የሀገር ውስጥ ዜና

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር ጉዞ ዋነኛ አካል ነው – ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

By Hailemaryam Tegegn

June 21, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር ጉዞ ዋነኛ አካል ነው አሉ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የኮንታ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በዛሬው ዕለት መርቀው ስራ አስጀምረዋል፡፡

ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ማዕከሉ የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ጣራ ሥር በማሰባሰብ የተገልጋዮችን ጊዜና ወጪ የሚቆጥብ ነው፡፡

መሶብ አንድ ማዕከል የሀገሪቱ የዲጂታል ሽግግር ጉዞ ዋነኛ አካል መሆኑን ጠቅሰው፥ የመንግሥትን አሰራር ለማዘመን፣ የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን ለማጠናከርና የሕዝብ አገልግሎትን ለማላቅ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

ማዕከሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል ነው ያሉት፡፡

የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች ካለፉት ጊዜያት በተሻለ ሁኔታ የምንመልስበትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በውጤታማነት የምንፈታበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡

መንግሥት ለሕዝቡ የገባውን ቃል በተግባር ለመፈጸም በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፥ በቀጣይም የሕዝቡን ጥያቄዎች በተጨባጭ የሚመልሱ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።