አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አዲስ የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ልምምድ ስር እየሰደደ መምጣቱ የታየበት ነው አሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ማሳወቂያ መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ የምርጫ ውግንና እንዳለው መንግስት የተረዳበት ነው፡፡
ከአምስት አመት በፊት ከተደረገው ጠቅላላ ምርጫ አዳዲስ ፖለቲካዊ እውቀቶች መቅሰም ተችሏል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እነዚህ የፖለቲካ ልምምዶች ስር እየሰደዱ መምጣታቸውን ተመልክተናል ብለዋል፡፡
ምርጫው ሰላምና እፎይታን እንደሚያረጋግጥ ሕዝቡ መረዳቱ እንዲሁም ሕዝብ የምርጫ ውግንና እንዳለው መንግስት መረዳቱ፣ በምርጫው ወቅት የተሸንራሸሩ ፖሊሲዎች ግልፅ መሆናቸው ስኬታማ ምርጫ እንዲካሄድ ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ምርጫው የኢትዮጵያ ህዝብ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ጥሪቱን ያወጣበት፣ ብሩህነት፣ ፍቅር እና እርስ በእርስ መተሳሰብ የታየበት እንደነበር ጠቅሰው ለመላው ኢትዮጵያውያን ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ሕዝቡ ይሁንታውን እና አመኔታውን የሰጣችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች፣ ኃላፊነታችሁን በፀጋ በመቀበል ለሀገር ልማትና እድገት ልትሰሩ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የምርጫ ትልቁ በረከት ለሀገር የሚኖረው ዘላቂ እድገትና መረጋጋት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ምርጫው በኢትዮጵያ ሰላምና ዴሞክራሲን ለማስፈን ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡
ከምርጫ ውጭ ስልጣን ለመያዝ የሚሞክሩና የቆየ የስልጣን ናፍቆት ያላቸው ቡድኖች ቢኖሩም፤ የዘመኑ ፖለቲካ ዴሞክራሲ፣ ቋንቋው ደግሞ መምረጥና መመረጥ ብቻ በመሆኑ እነዚህ ቡድኖች መንገዳቸውን እንዲያስተካክሉ መክረዋል፡፡
ኃይል ስልጣን ለመያዝ መሞከር የህዝብ መከራና የእድገት ሳንካ ከመሆን ውጭ የሚያመጣው ለውጥ የለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ በኢትዮጵያ በኃይል ስልጣን መያዝ እንደማይቻል አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ