ሰላም! እንደምን አደራችሁ?
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሀገር ግንባታ ምሰሶ…
በኢትዮጵያ ከሚከናወኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶች ውስጥ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አንዱ ነው፡፡የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አብሮነትን፣ መተሳሰብ እና መረዳዳትን ከማጎልበቱ ባለፈ የሕሊና እርካታ የሚገኝበት መልካም ተግባር ነው፡፡
በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከተለመደው የዕለት ተዕለት መረዳዳት ባለፈ ሀገር በቀል አቅምን የሚያንቀሳቅስ ትልቅ ብሔራዊ ንቅናቄ እየሆነ መጥቷል፡፡
ይህ ንቅናቄ የሕዝብ ለሕዝብ መተሳሰብን የሚያጠናክር፣ የሀገር አንድነትን የሚያጸና እና የወጣቱን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳይ ዋነኛ መድረክ ሲሆን ÷ በዚህም በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ወገናቸውን የሚያገለግሉበት መንገድ መፍጠር ተችሏል።
ዜጎች የአቅመ ደካሞችን ቤት መጠገን እና መገንባት፣ ደም መለገስ፣ በችግኝ ተከላ መሳተፍን ጨምሮ ከ14 በላይ በሚሆኑ የአገልግሎት ዘርፎች በመሳተፍ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ባሕል አድርገው እያሳደጉ ይገኛሉ።
እነዚህ ተግባራት በማሕበረሰቡ ውስጥ ያሉትን ክፍተቶች በመሙላት ረገድ የማይተካ ሚና አላቸው፤ ይህ አገልግሎት የመንግሥትን የልማት ሸክም ከመቀነስ ባለፈ ጥልቅ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን የሚያጠናክር ነው።
ወጣቶች ከሚኖሩበት አካባቢ እንዲሁም ከዚያ አልፈው በሌሎች አካባቢ ጭምር የተለያየ ቋንቋ እና ባህል ካላቸው ማሕበረሰቦች ጋር በጋራ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት በሕብረሰተቡ መካከል ጠንካራ የመተሳሰብ ድልድይ እንዲገነቡ አስችሏቸዋል።
በአስቸጋሪ የክረምት ወራት የአንዱ ችግር የሌላውም ህመም መሆኑን በመረዳት እርስ በርስ መደጋገፍ የዘመናት አብሮነትን በማደስ ኢትዮጵያዊነትን በጽኑ መሠረት ላይ የሚያቆም ተግባር ሲሆን÷ መተሳሰብ፣ ክፉ ቀናትን በጋራ የማለፍ ባህልን በማዳበር የሀገርን ሰላምና አንድነት በላቀ ደረጃ ያጠናክረዋል።
አሁን ላይ ወጣቱ ትውልድ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የሚያሳየው ከፍተኛ ተነሳሽነት፣ ስለ ሀገሩ የሚያስብና ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ እየተፈጠረ መሆኑን ማረጋገጫ ነው።
ወጣቶች እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን ያለምንም ክፍያ ለሀገራቸው በመስጠት፣ የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያን በገዛ እጃቸው በመገንባት ለሀገር ዕድገት ያላቸውን ቀዳሚ ተዋናይነት ሚና እየተወጡ ይገኛሉ።
ይህ ንቅናቄ ማሕበራዊ ውበት ብቻ ሳይሆን፣ የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ጫና በከፍተኛ ደረጃ ማቃለል የቻለ ነው ፤ዜጎች በሚሰጡት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ብቻ ከመንግሥት እና ከሕብረተሰቡ ሊወጣ የነበረን በቢሊየን የሚቆጠር ሀብት ማዳን ተችሏል።
በኢትዮጵያ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የሚታየው የዜጎች ከፍተኛ ተነሳሽነት በተለይም ወጣቱ ትውልድ የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያን በገዛ እጁ የሚቀርጽ መሆኑን የሚያሳይ ነው ፤በጎ ፈቃድ ብሔራዊ አንድነትን በማጥበቅ እና ሕዝብን ከሕዝብ በማስተሳሰር ረገድ የሚጫወተው ሚና በቀላሉ የሚገመት አይደለም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ጎሮ ወረዳ ያሳለፍነው ሰኔ11 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል፡፡
በዚህ ወቅትም ሀገራችንን በጋራ ማንሳት የምንችለው አንዳችን ለሌላችን እጃችንን ስንዘረጋ ብቻ ነው፡፡ የክረምቱ ወቅት ሲደርስ፣ እኛም ለወገኖቻችን የምንዘረጋው የደግነት እጅ አብሮ ይጀግናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በተያዘው ክረምት ወጣቶች ዕውቀታቸውንና ጉልበታቸውን፤ ባለሃብቶች ደግሞ ሃብታቸውን በማዋጣት የዐቅመ ደካማ ወገኖችን ቤት በመገንባት፣ ማዕድ በማጋራት፣ በደም ልገሳ፣ በአረንጓዴ ዐሻራና በሌሎች በጎ ሥራዎች መሳተፍ ይጠበቅባዋል፡፡
የመንግሥት ተቋማትም በቁጠባ ከሚጠቀሙት ሀብታቸው በማዋጣት ይህንን የበጎ አድራጎት ልምድ የማስፋት እና ወደ ላቀ ባህል ደረጃ ለማሳደግ በትኩረት መስራት አለባቸው፡፡
ስለሆነም ይህንን መልካም ዕሴት ይበልጥ ተቋማዊ በሆነ መንገድ በማደራጀትና የወጣቱን ብሎም የባለሃብቱን ቁርጠኝነት በዘላቂነት በመደገፍ፣ የሀገሪቱን የነገ ጉዞ ብሩህ ማድረግ የሁሉም አካላት የጋራ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ እውነተኛ ብልጽግናም ሆነ የሀገር ግንባታ እውን የሚሆነው ትልቅ የሀገሪቱ ሃብት የሆኑት ከ130 ሚሊየን በላይ ዜጎች ጉልበታቸውን፣ ሃብታቸውንና እውቀታቸውን ደምረው መጠቀም ሲችሉ ነው፡፡