ስፓርት

በዓለም ዋንጫው አርጀንቲና ከኦስትርያ እንዲሁም ኖርዌይ ከሴኔጋል የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል

By abel neway

June 22, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 12ኛ ቀኑን በያዘው 23ኛው ዓለም ዋንጫ ዛሬ ምሽት አርጀንቲና ከኦስትሪያ የምታደርገው ጨዋታ ይጠበቃል፡፡

በዳላስ ስታዲየም ምሽት 2 ሰዓት ላይ በሚደረገው ጨዋታ አርጀንቲና ካሸነፈች ወደ ጥሎ ማለፉ መግባቷን ታረጋግጣለች፡፡

በሌላ በኩል በውድድሩ 16 ግቦችን በማስቆጠር ከጀርመናዊው ሚሮስላቭ ክሎስ ጋር ክብረ ወሰን የተጋራው ሊዮኔል ሜሲ በዚህ ጨዋታ ግብ ማስቆጠር ከቻለ በዓለም ዋንጫ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ መሆን ይችላል፡፡

በሌላ የውድድሩ መርሐ ግብር እኩለ ለሊት 6 ሰዓት ፈረንሳይ ከኢራቅ ጋር ትጫወታለች፡፡

በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ ሴኔጋልን 3 ለ 1 ያሸነፈችው ፈረንሳይ፤ የዛሬውን መርሐ ግብሯን በድል ማጠናቀቅ ከቻለች ጥሎ ማለፉን ትቀላቀላለች፡፡

ሊነጋጋ ሲል ኖርዌይ ከሴኔጋል የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ሲሆን፤ ኖርዌይ የምታሸንፍ ከሆነ ወደ ጥሎ ማለፉ መግባቷን ታረጋግጣለች።

በሴኔጋል በኩል መሸነፍ ከውድድሩ የሚያሰናብታት ይሆናል፡፡

ዮርዳኖስ ከአልጄሪያ ነገ ጠዋት 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡