የሀገር ውስጥ ዜና

እርካታን የፈጠረ አገልግሎት….

By Abiy Getahun

June 22, 2026

በመንግሥት አገልግሎት ላይ የተገልጋዮችን እርካታ መፍጠር የአንድን ተቋም ውጤታማነት እና ተዓማኒነት መለኪያ ቁልፍ መሣሪያ ነው።

የመንግሥት አገልግሎትን ማዘመን የመጨረሻ ግቡ የዜጎችን እርካታ ማረጋገጥ እና በመንግሥት ላይ ያለቸውን እምነት መገንባት ነው፡፡

አገልግሎቶች ዘመናዊ ሲሆኑ እንግልት፣ አድልዎ እና አላስፈላጊ ወጪዎች ይቀንሳሉ፤ ይህም በቀጥታ የተገልጋይ እርካታን ይፈጥራል፡፡

መንግሥት በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን በማዘመን የዜጎችን እርካታ ለመፍጠር እየሰራ ነው፡፡

ስራዎቹም ተገልጋይ ተኮር፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ያቀናጁ፣ የሰው ኃይል ክህሎትንና አመለካከትን የለወጡ እና ቀጣጥነት ያላቸው ማሻሻያን የሚተገብሩ ናቸው፡፡

የወረቀት አልባ አሠራር የሰነዶችን ትክክለኛነት በሲስተም በማረጋገጥ ተገልጋዩ ባልተገባ መንገድ ጊዜውን እንዳያባክን እና ለፎቶ ኮፒ እና ለመሰል ወጪዎችም እንዳይጋለጥ ያግዛሉ፡፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአጭር ጊዜ በሁሉም ክልሎች እየተስፋፋ ይገኛል፡፡

ይህም ዜጎች በመንግሥት አገልግሎት ላይ እርካታ እንዲኖራቸው እያደረገ ነው፡፡ በመሶብ ግልጸኝነት የተላበሰ መረጃና አገልግሎት የመስጠት፣ የአሰራር ሂደቶችን የማቃለል፣ የሰራተኞችን ትጋት የመጨመር፣ ቅሬታዎች ሲኖሩ ቶሎ የመፍታት፣ የስራ አካባቢን ለሰራተኞች እና ለተገልጋዮች ምቹ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፡፡

ተገልጋዮች ተራቸውን እስኪጠብቁ ድረስ መቀመጫ ወንበር፣ ንጹሕ የመጸዳጃ ቤት እና ለአረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ምቹ መተላለፊያ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ የትኛው ቢሮ ወይም መስኮት ምን አገልግሎት እንደሚሰጥ የሚያሳዩ ግልጽና በቀላሉ የሚታዩ ምልክቶች ተለጥፈውላቸዋል፡፡

ቀላልና ግልጽ መመሪያዎች ውስብስብ አሠራሮችን እና ረዣዥም የቅጽ መሙላት ሂደቶችን በማስቀረት አገልግሎቱን ለሁሉም ሰው ቀላል እያደረገው ይገኛሉ።

መንግሥት በዲጂታል አማራጮች የሚሰጣቸው አገልግሎቶች የ24/7 ተደራሽነት አላቸው፡፡ በዚህም ተገልጋይ የመንግሥት የሥራ ሰዓት እስኪከፈት ሳይጠብቅ፣ ዜጎች በፈለጉት ሰዓትና ቦታ (በሞባይል ወይም በኮምፒውተር) ለአገልግሎት ማመልከት እንዲችሉ አድርጓል፡፡

አገልግሎት ለማግኘት ወደ መሶብ ጎራ የሚል ሰው ቅድሚያ ስለአገልግሎቱ መረጃ ያገኛል ማለት ነው፡፡ ይህም ግልፀኝነት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡

በዚሁ መሠረት አንድ አገልግሎት ምን ምን ሰነዶችን እንደሚጠይቅ፣ ምን ያህል ክፍያ እንዳለው እና ስንት ደቂቃ ወይም ቀን እንደሚፈጅ ለተገልጋዩ በግልጽ በቦርድ ወይም በዌብሳይት የማሳወቅ ስራ እየተሰራ ነው፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ ተገልጋዩ ያስገባው ማመልከቻ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ በስልክ አጭር መልዕክት (SMS) ወይም በኢሜይል በየጊዜው መረጃ እንዲደርሰው ይደረጋል፡፡ ይህም እንግልትን የሚያስቀርና እርካታን የሚፈጥር ነው፡፡

የአሠራር ሂደቶችን በማቅለል አላስፈላጊ ቢሮክራሲን በመቀነስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፍቱን ሆኗል፡፡

አንድን ጉዳይ ለማስፈጸም መፈረም ያለባቸውን የኃላፊዎች ብዛት እና መሄድ ያለባቸውን ቢሮዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል፡፡

በአንድ ማዕከል አገልግሎት ተገልጋዮች ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች መረጃዎችን ከመሰብሰብ ይልቅ ሁሉንም ጉዳዮቻቸውን በአንድ መስኮት እንዲጨርሱ እያደረገ ነው፡፡

የዚህ የዲጂታል ዘመን ሠራተኞች ተገልጋዩን በፈገግታ፣ በትሕትና እና በአጋዥነት ስሜት እየተቀበሉ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡

አገልግሎት ሰጪ ሠራተኛው ስለሚሠራው ሥራ በቂ እውቀትና ክብር ኖሮት እንዲሰራ እየተደረገ ስላለ ተገልጋዩ በሚሰጠው ፈጣን ምላሽ እርካታ ተፈጥሮለታል፡፡

ከቀድሞዎቹና ነባር የመንግሥት አገልግሎቶች አንጻር ሲታይ ፍጹም ተጠያቂነትን የሚያሰፍን እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ነው፡፡

እንግልት የሚፈጥሩ ወይም ተገቢ ያልሆነ ጠባይ የሚያሳዩ ሠራተኞች አይኖሩም፡፡የአገልግሎት ሰጪነት ባህል እየዳበረ መጥቷል፡፡

የመንግሥት ሠራተኞች ራሳቸውን እንደ ገዥ ሳይሆን እንደ አገልግሎት ሰጪና እንደ ባለሙያ የሚያዩበትን አመለካከት እየተፈጠረ ነው፡፡

ተገልጋዮች ችግር ገጥሞናል ብለው ካሰቡ በነፃ ስልክ መስመር፣ በቅሬታ ሳጥን ወይም በዲጂታል መተግበሪያ በቀላሉ ቅሬታቸውን የሚያቀርቡበት ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡

አሰራሩ ለቀረቡ ቅሬታዎች በአጭር የጊዜ ገደብ መፍትሔ የመስጠት እና የተወሰደውን እርምጃዎችን ለቅሬታ አቅራቢው የማሳወቅ ሂደትም አለው፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ አገልግሎትን ዲጂታላይዝ በማድረግ የዘመነ የመንግሥት አገልግሎት በአዲስ አበባ እና በክልሎች ጭምር መስጠት ጀምራለች፡፡ ይህም የአገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ ተደራሽ እና ከአድልዎ የጸዳ እያደረገ ይገኛል፡፡

ኑ፤ ሀገር እንገንባ!