አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህራን የሕዝብ ድምጽ ያገኘው እና መንግሥት የመመስረት ዕድል የተሰጠው ብልጽግና ፓርቲ የተጣለበትን አደራና ኃላፊነት በሚመጥን ቁመና ሕዝቡን በቅንነት ማገልገል አለበት አሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትናንትናው ዕለት ይፋ ባደረገው የማጠቃለያ ውጤት መሠረት 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች በተሳተፉበት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ 17ቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ አግኝተዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት በመስከረም ወር ላይ አዲስ መንግሥት የመመስረት ዕድል ማግኘቱን ቦርዱ አሳውቋል።
ይህንን አስመልክቶ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉ የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህራን፤ የሚመሰረተው መንግሥት የሕዝብ አደራ በመወጣት የተጀመሩ ስራዎችን በማስቀጠል ሀገርን ማሻገር አለበት ብለዋል።
መምህር ካሚል ከድር እንዳሉት÷ ጠቅላላ ምርጫው በመራጮች፣ በተሳታፊዎች እንዲሁም በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ካለፉት ዓመታት እጅግ የላቀና ሰላማዊ እንደነበር ጠቅሰዋል።
ምርጫው ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ እንድትሸጋገር ትልቅ ተስፋ የሰጠ ነው ብለዋል።
የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችንና የተጀመሩ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸው፤ በኢኮኖሚ፣ በልማት፣ በሰላምና በሀገራዊ መግባባት ላይ የተጀመሩ ስራዎችን በማስቀጠል በፍጥነት መራመድ እንደሚገባት አብራርተዋል።
ሌላኛው መምህር ሙጂብ አብደላ በበኩላቸው÷ በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው የስልጣን ባለቤትነት መርህ መሠረት ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ የሚበጀውን የመረጡበትና ኢትዮጵያውያን ያሸነፉበት ሂደት መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም ከፍተኛ የሕዝብ ድምጽ ያገኘውና መንግሥት የመመስረት ዕድል የተሰጠው ብልጽግና ፓርቲ የተጣለበትን ታላቅ አደራና ኃላፊነት በሚመጥን ቁመና ሕዝቡን በቅንነት ማገልገል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የሕዝብን ጥያቄዎች በወቅቱ መመለስና የሕግ የበላይነትን ማስፈን እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ መምህርት መቅደስ መስፍን ናቸው።
የኑሮ ውድነትን ማቃለልና የዜጎችን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ማረጋገጥ እና የተጀመሩ ልማቶችን ከግብ ለማድረስ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
በዮናስ ጌትነት