አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በድህረ ምርጫ ወቅት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያሳዩት ጨዋነት ምርጫው ፍፁም ሰላም ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስችሏል አለ የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ፡፡
ምክር ቤቱ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም መጠናቀቅን ተከትሎ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፏል።
የጋራ ምክር ቤቱ ያስተላለፈው መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-
ከአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የተሰጠ የእንኳን ደስ አላችሁ መግለጫ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው ውጤት መሰረት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላማዊና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተጠናቆ የብልጽግና ፓርቲ አብላጫ ድምጽ በማግኘት ማሸነፉ ይታወቃል። የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ይህ ምርጫ የከተማችንም ሆነ የሀገራችንን የፖለቲካ ብስለትና የሕዝባችንን የሉዓላዊነት ስልጣን ያረጋገጠ ታሪካዊ መድረክ መሆኑን በጽኑ ያምናል። በመሆኑም በሕዝብ ነፃ ውሳኔ አሸናፊ ለሆነው ለብልፅግና ፓርቲ እና በውድድሩ ተሳትፋችሁ የምክር ቤት ወንበር ላገኛችሁ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰማንን ልባዊ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት በጋራ ምክር ቤቱ ስም እናስተላልፋለን።
ይህ ታሪካዊ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅና የሀገራችን የዲሞክራሲ ባህል እንዲጎለብት በውድድሩ የተሳተፉ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ላበረከቱት አወንታዊና ታሪካዊ አስተዋጽኦ የጋራ ምክር ቤታችን የላቀ ምስጋናውን ያቀርባል። በምክር ቤታችን ስር የሚንቀሳቀሱም ሆኑ በምርጫው የተሳተፉ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሂደቱ ላሳዩት ከፍተኛ የፖለቲካ ጨዋነት፣ ለሰላማዊ የሃሳብ ፉክክርና ለሕግ የበላይነት መገዛት የሚደነቅ ሲሆን፣ ይህ የሰለጠነ አካሄድ ለዜጎች ሰፊ የአማራጭ አድማስ ከመፍጠሩም በላይ ሂደቱ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በነፃነትና በሰላማዊ መንገድ ወጥተው የሰጡትን ድምፅና ያሳዩትን ምርጫ በሙሉ ልብ እየተቀበልን፣ ለሕዝብ ድምፅ ያለንን ፍጹም ክብርና እውቅና እናረጋግጣለን።
የምርጫው ምዕራፍ በተሳካ ሁኔታ ቢጠናቀቅም፡ የሀገር ግንባታ እና የሕዝብ አገልግሎት ቀጣይነት ያለው የጋራ ሃላፊነት በመሆኑ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። አሸናፊው የብልፅግና ፓርቲ የከተማችንንና የሀገራችንን ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ለማረጋገጥ በሚያደርገው ዘርፈ ብዙ ጥረት ላይ የጋራ ምክር ቤቱ በነቃ ተሳትፎ፡ በገንቢ ሂስና በአማራጭ ሃሳቦች አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል።
በድጋሚ ለብልፅግና ፓርቲ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም በውድድሩ ተሳተፋችሁ የምክር ወንበር ያገኛችሁ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እንኳን ደስ ያላችሁ እያልን መላው: የከተማችን ነዋሪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ባለድርሻ አካላት ለሰላማዊው የምርጫ ሂደት ስኬት ላደረጉት ታሪካዊ አስተዋጽኦ የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የላቀ ክብርና ምስጋናውን ይገልጻል።
የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ