የሀገር ውስጥ ዜና

ፕሬዚዳንት ታዬ ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጋር ተወያዩ

By Mikias Ayele

June 22, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር በርሃም ሳሊህ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡

ውይይቱን አስመልክቶ በርሃም ሳሊህ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ከፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ውይይቱ ኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞችን በማስተናገድ ረገድ ለምትጫወተው ወሳኝ ሚና ድርጅታቸው ያለውን አድናቆትና እውቅና ለመግለጽ ትልቅ አጋጣሚ መፍጠሩን ገልጸዋል።

በተለይም ሀገሪቱ ስደተኞችን በብሔራዊ ሥርዓቱ ውስጥ ለማካተትና በሰብአዊ ርዳታ ላይ ብቻ ጥገኛ እንዳይሆኑ ለመርዳት ይፋ ያደረገችውን የማካተት ፍኖተ ካርታን በአብነት መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በፍኖተ ካርታው የትግበራ ሂደት ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ያረጋገጡ ሲሆን፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የጋራ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል ኮሚሽነር በርሃም ሳሊህ ኢትዮጵያ በቅርቡ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት በማጠናቀቋ ‘የእንኳን ደስ አላችሁ’ መልዕክት አስተላልፈዋል።