የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በኮፕ32 ጉባኤ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ቀጣይነትን የሚያረጋግጥ ስራ ታከናውናለች – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

By sosina alemayehu

June 23, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በምታዘጋጀው የኮፕ32 ጉባኤ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ቀጣይነትን የሚያረጋግጥ ስራ ታከናውናለች፡፡

ቻተም ሃውስ የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም “በተከፋፈለ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ የኮፕ ጉባኤዎችን አስፈላጊነት ማጉላት” በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የአየር ንብረት ሳምንት የውይይት መድረክ በለንደን ተካሂዷል፡፡

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ የምታዘጋጀው 32ኛው ጉባኤ ቀዳሚ ተግባራት በቱርክና አውስትራሊያ በጋራ ከሚዘጋጀው የኮፕ31 ውጤቶች በመነሳት ቀጣይነትን ማረጋገጥ ነው።

ይህ አካሄድ ከቀደሙት ሀገራት ጋር በቅንጅት በመስራት የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲን ማጠናከር የሚለውን የመደመር መርህ እንደሚያንጸባርቅ አፅንኦት ሰጥተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ጥበቃ ረገድ ጠንካራ ርዕይና ባለፉት ስምንት ዓመታት በፖሊሲ ተደግፈው በተከናወኑ ተግባራት የተመዘገቡ ስኬቶችን አብራርተዋል።

በመድረኩ የኮፕ30 ፕሬዚዳንት አንድሬ ኮሬያ እንዲሁም የኮፕ31ን የወከሉት የቱርክ የአካባቢ፣ የከተማ ልማት እና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ተገኝተዋል።